አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዞኑን ሰላም በማስቀጠል ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ይሰራል አሉ በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ ረሻድ ከማል (ዶ/ር)፡፡
ረሻድ ከማል (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት የተያዘውን የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥና ሀገራዊ ምርታማነትን የማሳደግ ግብን ለማሳካት በኦሮሚያ ክልል በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ተግባራዊ የሆነው አዲሱ አደረጃጀት ለሁሉንተናዊ የልማት መረጋገጥ የላቀ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን በሊሙ ኮሳ ወረዳ በክላስተር የለማ ሩዝ ምርት በኮምባይነር መሰብሰብ ተጀምሯል፡፡
በዞኑ በዚህ ዓመት ከሩዝ ምርት ከ23 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ አመልክተዋል፡፡
በዞኑ ከፍተኛ የልማት አቅም እንዳለና በሁሉም የግብርና ኢንሼቲቮች ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲሱ አደረጃጀት አጠቃላይ የልማት አቅም ወደ ሥራ በማስገባት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በማጠናከር ረገድ አዎንታዊ ሚና አለው ብለዋል።
የዞኑን ሰላም በማስቀጠል ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በወርቅአፈራው ያለው

