Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከኢትዮጵያ መንግሥት የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ጋር የተቀራረበው የአይ ኤም ኤፍ ትንበያ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በ2019 በጀት ዓመት 10.2 በመቶ እንደሚድግ ያስቀመጠው ግምት ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ትንበያ ጋር የተቀራረበ ነው፡፡
አይ.ኤም.ኤፍ ይፋ ባደረገው በፈረንጆቹ የ2026 የዓለም የኢኮኖሚ ትንበያ መሰረት፣ የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ዕድገት 9.2 በመቶ እንደሚሆን ትንበያውን አስቀምጧል።
ይህ መረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት ካስቀመጠው የ10.2 በመቶ ግምት ጋር በእጅጉ የሚቀራረብ መሆኑ የሀገሪቱን ፈጣን የኢኮኖሚ አቅጣጫ አስተማማኝነት በግልጽ ያሳያል።
የትንበያዎቹ መቀራረብ መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች ያከናወናቸው የልማት ስራዎች ስኬትን የሚያሳይ ነው፡፡ በግብርናው ዘርፍ የተከናወኑ የማምረቻ ማሻሻያዎች፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ አፈፃፀሞች፣ እንዲሁም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ሌሎችም ትላልቅ የልማት ሜጋ ፕሮጀክቶች ለኢኮኖሚው መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
መንግስት በሀገራዊ የልማት እቅዶቹ ያስቀመጣቸው ግቦች እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ያስቀመጠው 9.2 በመቶ ግምት እጅግ መቀራረባቸው፣ የሀገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲዎች በትክክለኛ አፈጻጸም ሂደት ላይ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።
በሁለቱ ትንበያዎች መካከል ያለው ልዩነት መጥበብ ስለ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት አቅጣጫ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው። የኢትዮጵያ መንግስት ያስቀመጠው የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ እና የውጭ ተቋማት ትንበያዎች መቀራረብ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች በሀገሪቱ ገበያ ላይ ያላቸውን እምነት ከፍ እንዲል ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪ የኢኮኖሚው አቅም ከውጭ ግምት ጋር ተቀራራቢ መሆኑ የፖሊሲ አፈፃፀሙን አስተማማኝነት በማጠናከር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ቁልፍ እገዛ ያደርጋል።
ባለፈው ዓመት 9.2 በመቶ እድገት ያስመዘገበው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁንም ዕድገቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፣ ለፈጣንና ዘላቂ ሀገራዊ ብልጽግና ጉዞ አስተማማኝ መሰረት የሚጥል ነው።
Exit mobile version