አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሀገራዊ መግባባት የሚረዱ ምክረ ሃሳቦችን ለመተግበር መንግሥት ዝግጁነቱን መግለጹ ለውጤታማነቱ መሰረት ነው አሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር)፡፡
ኮሚሽነሩ እንዳሉት÷ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድነት ተሰባስበው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰፊው የመከሩበት ነው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ አመለካከቶችና ልዩነቶች ቢኖሯቸውም ምክክር ለሀገሪቱ ዘላቂ እድገትና ሰላም እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ላይ የጋራ አቋም መያዛቸውን ገልጸው በዚህ ታሪካዊ የምክክር ሂደት ውስጥ 42 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በንቃትና በባለቤትነት መሳተፋቸውንም ተናግረዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች መካከል ወደ ሰላማዊ መንገድ በመመለስ አጀንዳዎችን ያቀረቡ መኖራቸውን በማንሳት የምክክር ሂደቱ የሁሉም ወገኖች ድምፅ የተሰማበት፣ አሳታፊነቱንና አካታችነቱን ያረጋገጠ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ መመዝገቡን አስገንዝበዋል።
የመንግሥት ተቀባይነትና ሕዝባዊ አመኔታ መጎልበት ለአንድ ሀገር ዘላቂ ሰላም፣ ማህበራዊ መረጋጋት አና አጠቃላይ እድገት እውን መሆን መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
ሀገራዊ መግባባትን ለማስፈንና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ምክረ ሀሳቦችን ለመተግበር መንግሥት ዝግጁነቱን ማስታወቁ ለውጤታማነቱ ትልቅ እርምጃ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሂደቱ የምክረ ሀሳቦችን የትግበራ ሂደት ለመከታተል የሚያስችል አጠቃላይ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
የክትትልና ቁጥጥር ሥራው ስኬታማ ይሆን ዘንድ ምክር ቤቱ ከተለያዩ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት ጋር በትብብር ይሰራል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

