Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ – ለማይበገር የሳይበር ደኅንነት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከመሠረተባቸው ምሰሶዎች መካከል ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አንዱ ነው።

በዚህም ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች በተለይም በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ አስደናቂ ውጤት መጥቷል። በዘርፉ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበ ቢሆንም የሳይበር ደኅንነት ሥጋት መኖሩ አልቀረም።

7ኛው አገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ወር “ንቁ ዜጋ፤ ደኅንነቷ ለተጠበቀ አገር” በሚል መሪ ቃል ከጥቅምት 1 እስከ 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።

የወሩ መከበር ዋና ዓላማ የኅብረተሰቡንና የተቋማትን የሳይበር ደኅንነት ንቃት በማጎልበት፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ጉዞን ማሳካት ነው።

በአሁኑ ወቅት የሳይበር ጥቃት ሥጋቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፉ፣ መልካቸውን እየቀየሩ፣ ይበልጥ ውስብስብና አደገኛ እየሆኑ መጥተዋል።

በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች፣ የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት እና የመረጃ ጦርነቶች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ሊፈጥሩ ይችላሉ።

በ2018 ዓ.ም ብቻ ከ71 ሺሕ በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የብሔራዊ የሳይበር ድንገተኛ አደጋ ምላሽ መስጫ ማዕከል (Ethio CERT) በኩል ሪፖርት ተደርገዋል።

ይሁን እንጂ ኢመደአ 24/7 በሚያደርገው ቋሚ ክትትልና ቁጥጥር ጥቃቶቹ በአገራችን ላይ ጉዳት እንዳያደርሱና የዲጂታሉ ዳር ድንበር እንዲጠበቅ በስፋት እየተሠራ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ እና በአሠራር ሥርዓት ግንባታ ረገድ ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል።

የኢመደአ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በሳይበር ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች ማብቃት፣ አገር በቀል የሆኑ የደኅንነት ቴክኖሎጂዎችን ማበልጸግ እንዲሁም የቁጥጥር ማዕቀፎችን መዘርጋት ተችሏል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የተሳኩት የኢንተርኔት ተጠቃሚነት መስፋፋት፣ የቴሌኮም ዘርፉ ለውድድር መከፈት፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች መስፋፋትና የመንግሥት አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ የማቅረብ እርምጃዎች ለዲጂታል ሽግግር መሠረት ጥለዋል።

አሁን ላይ እየተተገበረ የሚገኘውን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እውን ለማድረግና የቴክኖሎጂ ዕድገትን የአገር አቀፍ ብልጽግና ወሳኝ ዓቅም ለማድረግ በሁሉም መስክ እየተሠራ ነው።

የዲጂታል ምኅዳሩን ከሳይበር ሥጋቶች መጠበቅ የዲጂታል ሉዓላዊነት፣ የዜጎችን ደኅንነትና የልማት ጉዞን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው። በመሆኑም የዲጂታል ምኅዳሩን የሚጠብቅና ደኅንነቱን የሚያጠናክር ንቁና ኃላፊነት የሚሰማው የሰው ኃይል የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

Exit mobile version