Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ባሕር በር፤ የኢትዮጵያ የሕልውና ጥያቄ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቦቿ የቅንጦት ወይም የፖለቲካ ምርጫ ሳይሆን የሕልውና፣ የኢኮኖሚ ደኅንነት እና የትውልድ ቀጣይነት መሠረታዊ ጥያቄ ነው።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ይዛ በዓለም ላይ ካሉ ወደብ አልባ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ መሆኗ የባሕር በር ፍላጎቷን የሞትና የሽረት ጉዳይ ያደርገዋል።

የባሕር በር ባለመኖሩ በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ አቅም ላይ ትልቅ ጫና የፈጠረ በመሆኑ የራስን የባሕር በር ማግኘት ወይም አማራጮችን ማስፋፋት የሕዝቡን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ ወሳኝ እርምጃ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የግብርና ምርቶችን በተወዳዳሪ ዋጋ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እንዲሁም እንደ ማዳበሪያ፣ ነዳጅ እና መድኃኒት ያሉ መሠረታዊ ሸቀጦችን በፍጥነትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማስገባት አስተማማኝ የባሕር በር መኖር ግድ ይላል።

በሌላ ሀገር ሙሉ ቁጥጥር ስር በሆነ አንድ የባሕር በር ላይ ብቻ ፍጹም ጥገኛ መሆን የሀገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት ለከፍተኛ ሥጋት ያጋልጣል።

በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድና በቀይ ባሕር አካባቢ የሚፈጠሩ ድንገተኛ የፖለቲካ ወይም የጸጥታ መዋዠቆች የሀገሪቱን የንግድ መስመር ሙሉ በሙሉ ሊዘጉ የሚችሉ በመሆናቸው ኢትዮጵያ የጸና አማራጭ የባሕር በር ሊኖራት ግድ ይላል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት የጎረቤት ሀገራትን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በሚነካ መልኩ የሚከናወን ሳይሆን በሰላማዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ እና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ላይ የተመሠረተ ነው።

ኢትዮጵያ ያላትን ታላቅ የሕዝብ ቁጥር፣ ሰፊ ገበያ እና እንደ አየር መንገድ፣ ቴሌኮምና ታዳሽ ኃይል ያሉ የልማት ድርሻዎችን ለጎረቤቶቿ በማጋራት የጋራ ብልጽግናን ለመፍጠር ትሻለች።

ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ የባሕር በር ፍላጎት ከታሪክ፣ ከኢኮኖሚና ከጂኦፖለቲካ አንጻር ፍጹም ፍትሐዊና መሠረታዊ ጥያቄ ነው።

ይህንን ፍላጎት በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ማሳካት የኢትዮጵያን ዕድገት ከማፋጠኑም በላይ፣ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትስስርና የሰላም መደላድል ይበልጥ እንዲጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በትዕግሥት ግዛቸው

Exit mobile version