Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ትብብራቸውን ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መከሩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9 ፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከአሜሪካ ግምጃ ቤት የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ምክትል ረዳት ሚኒስትር ኤሪክ ሜየር ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በታይላንድ ባንኮክ እየተካሄደ ከሚገኘው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን ባደረጉት ውይይት፤ የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ለማጠናከርና የሁለትዮሽ ትብብራቸውን የበለጠ ለማሳደግ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
በዚህም ማሻሻያውን ለማፋጠን የሚያስችሉ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፎችን ማሳደግ የሚቻልባቸው ጉዳዮች ተነስተዋል።
ሁለቱም ወገኖች የጋራ የልማት ግቦችን ለማሳካትና በቀጣናው ዘላቂ መረጋጋትን ለማስፈን መደበኛና ገንቢ የሆኑ ውይይቶችን አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል።
በተጨማሪም በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በኩል ለኢትዮጵያ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታም ውይይት መደረጉንም ባንኩ ገልጿል፡፡
ምክትል ረዳት ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያን የመዋቅራዊ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ አድንቀው፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ገንቢ የሁለትዮሽ አጋርነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
Exit mobile version