አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝበትን የዲፕሎማሲ ከፍታ በአንድ ጀምበር አላመጣችውም፡፡ ይልቁንም ለበርካታ ዓመታት በጥንቃቄ የገነባችው የስኬት ማማ ነው፡፡
ከጥንት የንግድና የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ጀምሮ እስከ ዘመናዊው የተባበሩት መንግሥታት እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ንቁ ተሳትፎ የነበራት ኢትዮጵያ ዛሬም ይህን ታሪኳን አስቀጥላ በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነትን አትርፋለች፡፡
የሀገራት ዲፕሎማሲ ጥንካሬ ከህዝቦች የለት ተዕለት እሴት ይመነጫል፡፡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የእንግዳ ተቀባይነት ፣ የሰላም፣ የትዕግስት፣ የታላቅነትና የአሸናፊነት ሥነልቦና ባለቤት ናቸው፡፡
የአፍሪካ ህብረት ድርጅት እንዲመሰረትና አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲወጡ፣ በዓለም መድረክ ድምፅ እንዲኖራቸው ዋጋ የከፈለችው ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ብሪክስ ባሉ የተለያዩ መድረኮች የአፍሪካውያን ድምፅ በመሆኗን ቀጥላች።
በመሆኑም በዲፕሎማሲው መስክ ያለው ከፍታ ከኢትዮጵያ ድንበር አልፎ ለአህጉር የሚተርፍ ነው ለማለት ያስችላል፡፡
ኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገራት ተሰባስበው የሚመክሩባትነ ውሳኔ የሚሰጡባቸው የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ሆናለች፡፡
በፍጥነት በሚለዋወጠው የዓለም የዲፕሎማሲ ምህዳር ውስጥ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር በሁለትዮሽና በባለ ብዙ ወገን መድረኮች በንቃት ተሳትፋለች፡፡ ሀገሪቱ ፈተናዎች ውስጥ በገባችባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ዲፕሎማሲያዊ አቅሟ በአግባቡ ተጠቅማለች አልፋቸዋለች፡፡
የውጪ ጫናዎች በሚገጥሙበት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር፣ ክብሩንና ሉዓላዊነቱንም ለማስከበር የሚያደርገው ቁርጠኝነትና ተጋድሎ አንዱ የዲፕሎማሲ አቅሟ መገለጫ ነው።
በህዝብ ንቁ ተሳትፎ የተገነቡት እንደ ህዳሴ ግድብ ፣ እንዲሁም ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎትና የውስጥ አቅም ከማሳየት ባሻገር ለዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ ትልቅ ሚና አላቸው።
ኢትዮጵያ በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ ከየትኛውም ቡድን ያልወገነ ገለልተኛ የዲፕሎማሲ አቋም ትከተላለች፡፡ የቀደሙ ወዳጆቿን አጥብቃ ከማስቀጠሏ ባሻገር እንደ ብሪክስ ባሉ ጥምረቶች ላይ ከተሳታፊነት አልፋ አጀንዳ በመቅረፅ ጭምር ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች።
ይህም ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር አዳዲስ እድሎችን የመጠቀም ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ተደርጎ ይወሰዳል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በውስጥ ጥንካሬና በህዝቦቿ የአይበገሬነት መንፈስ ብሔራዊ ጥቅሟን በማስከበር በዲፕሎማሲው መስክ ዕምርታ እያሳየች ትገኛለች።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በቤተልሔም ግርማ

