አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የ3ኛ ዙር መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት ዘጠኝ ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
የወቅቱ የመድረኩ አሸናፊ ፒኤስጂ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሜዳው ፓርክ ደ ፕሪንስ የስፔኑን ክለብ ባርሴሎናን ያስተናግዳል፡፡
የፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ በዚህ የውድድር ዓመት በሻምፒንስ ሊጉ ያደረጋቸውን ሁለቱንም ጨዋታዎች ድል አድርጓል፡፡
በአሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ የሚመራው ፒኤስጂ በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር መልካም ጅማሮ ላይ ይገኛል፡፡
ፒኤስጂ ባደረጋቸው ሁለት የሻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች 10 ግቦችን ተጋጣሚዎቹ ላይ አስቆጥሮ፤ የተቆጠረበት 3 ግብ ብቻ ነው፡፡
ዴምቤሌ፣ ክቫረትስኬሊያ፣ ዱዌ፣ ቪቲንሃ፣ ፌራን ቶሬስ እና ፋቢያን ሩሂዝ የመሳሰሉ ተጫዋቾች በፒኤስጂ በኩል የሚጠበቁ ተጨዋቾች ናቸው፡፡
የካታላኑ ክለብ ባርሴሎና በውድድር ዘመኑ በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ያደረጋቸውን ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
በላሊጋው እና በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ አስደናቂ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ባርሴሎና በዛሬው ጨዋታ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተጠባቂ ነው፡፡
በአሰልጣኝ ሃንሲ ፍሊክ የሚመራው ባርሴሎና ባደረጋቸው ሁለት የሻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቹ ላይ 9 ግቦችን አስቆጥሮ፤ የተቆጠረበት 2 ግብ ብቻ ነው፡፡
ላሚን ያማል፣ ራፊኒሃ፣ ሮድሪ፣ ፔድሪ፣ ፈርሚን ሎፔዝ እና ኦልሞ የመሳሰሉ ተጨዋቾች በጨዋታው ይጠበቃሉ፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ፒኤስጂ ሦስቱን ሲያሸንፍ፤ ባርሴሎና በአንዱ ድል አድርጎ፤ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡
ማንቼስተር ሲቲ ከኤኢኬ አቴንስ፣ ሊቨርፑል ከቪያሪያል፣ ስቱትጋርት ከአትሌቲኮ ማድሪድ፣ ሮማ ከስሎቫን ብራቲስላቫ፣ ፖርቶ ከፒኤስቪ እንዲሁም ናፖሊ ከቦዶ ግሊምት በተመሳሳይ ምሽት 4 ሰዓት ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡
ከእነዚህ ጨዋታዎች አስቀድሞ ምሽት 1 ሰዓት ከ45 ላይ ሳባህ ከቦርሲያ ዶርትሙንድ እንዲሁም ፌነርባቼ ከስላቪያ ፕራህ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

