አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የክልሉን ጸጋና አቅም በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል አሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይትምጌታ አስራት (ዶ/ር)።
ርዕሰ መስተዳድሩ ክልላዊ የግብርና ምርቶች ኤግዚቢሽን በዱራሜ ከተማ መርቀው ከፍተዋል፡፡
ይትምጌታ አስራት (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በግብርና ዘርፍ በቅንጅትና በትጋት መሥራት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የግብርና ሽግግሩን ለማፋጠን ወሳኝ ነው።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የልማት ሥራዎች በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር፣ ገበያ ተኮር የሆኑ ምርቶችን ማምረት እና ከዚህ በፊት በክልሉ በስፋት ይመረቱ ያልነበሩ ምርቶችን ማምረት መጀመሩ አበረታች ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ ኢኮኖሚ ውስጥ 53 በመቶ ድርሻ ያለው የግብርና ዘርፍ የምርት መጠንንና ጥራትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በበጋው የተቀናጀ የግብርና ንቅናቄ የክልሉንም ሆነ የሀገሪቱን የልማት ግቦች ለማሳካት ሁሉም አካላት በተሻለ ቅንጅትና ትጋት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው÷ ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ 27 የሚደርሱ የግብርና
ምርቶችን የሚያቀነባብሩ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች መገንባታቸውን ተናግረዋል።
የተቀናጀ የግብርና ሥራ ዓመታዊ የምርት ወቅቶችን ከሦስት ወደ አምስት ማሳደግ እንዳስቻለም ገልጸዋል።
በጌታቸው ሙለታ

