Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የትግራይ ክልል ሕዝብ የሚፈልገው ሰላምና ልማት ነው – ብ/ጄኔራል ገብረእግዝአብሔር በየነ (ወዲ አንጥር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ክልል ሕዝብ የሚፈልገው ሰላምና ልማት ነው አሉ የትግራይ ክልል የፌደራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር የጸጥታ እና ሰላም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዝአብሔር በየነ (ወዲ አንጥር)።

ብርጋዴር ጄኔራሉ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ውጊያውን ቢያቆመውም ህገ ወጡ ህወሓት ለዳግም ጦርነት ሲዘጋጅ በመቆየቱ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ፈቃደኛ እንዳልነበረ አስረድተዋል።

በዚህም ምክንያት የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ አስፈትቶ ወደ ሰላማዊ ህይወት የማመለስ (DDR) ሂደት በጥርጣሬ ታይቶ ሳይተገበር በመቅረቱ ወጣቱ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ብለዋል።

ህገ ወጡ ህወሓት ወጣቱን ወደ ሌላ ወታደራዊ ግጭት በመክተቱ ክልሉ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ውድቀት መዳረጉንና በአሁኑ ወቅት ክልሉ በርካታ ቁስለኛ፣ ተፈናቃይ እና የትምህርት እድል ያጡ ወጣቶች የበዙበት ሆኗል ነው ያሉት።

ወጣቶች ጊዜያቸውን በውትድርና ሳያባክኑ ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡና ህይወታቸውን እንዲያስተካክሉ ጥሪ በማቅረብ፣ የDDR መርሃ ግብር ለዘላቂ ሰላምና ለስራ እድል ፈጠራ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

ክልሉን ሲያመስ የነበረው ቡድን የትግራይን ህዝብ የማይወክል፣ ስልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል ክልሉ እንዲወድም ከሚፈልገው ሻዕቢያ ጋር የተቀናጀ እና ሀብት የዘረፈ ቡድን መሆኑ ተጋልጧል ብለዋል።

አሁን ላይ ወጣቱም ሆነ ህዝቡ ጦርነት የማይፈልግ በመሆኑ ቡድኑ በኃይል አሸንፋለሁ ማለቱ የቅዥት ያህል እንደሆነ እና ህዝቡም ከጎኑ እንደሌለ አመልክተዋል።

Exit mobile version