Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፖለቲካ ቁማር ያላራመዳቸው እግሮች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም ታሪክ ውስጥ የትኛውም ሀገር አያሌ ተፈጥሯዊ ሀብት፣ የበለጸገ የንግድ መስመር፣ ወይም ጠንካራ የኢንዱስትሪ መሰረት ቢኖረውም፤ መሪዎች ስልጣንን ለግልና ቡድናዊ ጥቅም ማዋል ሲጀምሩና የተሳሳቱ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ሲከተሉ ውድቀቱ አስከፊ ይሆናል።

አንድ ሀገር የኢኮኖሚና የማህበራዊ እድገት ባለቤት ሆኖ ለመቀጠል ጠንካራ ተቋማትና የህግ የበላይነት ያስፈልጉታል።

ሰላም፣ የንግድ ትስስርና የክልላዊ ትብብር ደግሞ የልማቱ ወሳኝ መደላድሎች ናቸው። በተጨማሪም አምራቹንና ወጣቱን ኃይል በሀገር ውስጥ የማቆየትና የመጠቀም አቅም ሊኖረው ይገባል።

እነዚህ መሰረታዊ ሀቆች በጎደሉበት ቦታ ሁሉ የቱንም ያህል የበለጸጉ ከተሞችና የባሕር በሮች ቢኖሩም፣ ሀገር ወደ ባዶነትና ውድቀት መውረዷ አይቀሬ ነው።

ይህንን ጥቅል እውነት በግልጽ ከሚያሳዩት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል ኤርትራ ግንባር ቀደሟ ናት።

ትናንት ከኢትዮጵያ ጋር  ሳለች በኢንዱስትሪና በንግድ እንቅስቃሴዋ ደማቅ የነበረችው ኤርትራ ዛሬ ሀገር ሆና በስልጣን ጥመኞች የተሳሳተ ፖለቲካዊ ቁማር ዕድገቷ ከስር መሰረቱ ተመናምኖ የኋሊት ጉዞ ላይ ትገኛለች።

ሕዝቧም የልማትና የሰላም ባለቤት ከመሆን ይልቅ የጦርነት፣ ስደትና ድህነት ሰለባ ሆኗል።

አስመራ በዘመናዊ ስነ-ሕንጻዎቿና በከተማ መዋቅሯ ትታወቅ ነበር፤ የምጽዋና የአሰብ ወደቦች ደግሞ የቀጣናው ዋና የንግድ ደምስሮች ነበሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በሰጡት ማብራሪያ እንዳመለከቱት፤ የኤርትራ አገዛዝ እኩይ አቅጣጫና የተሳሳተ የፖለቲካ ቁማር ሀገሪቱን ከስር መሰረቷ አምክኗታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ዛሬ ላይ አስመራ ተገቢውን ልማት አጥታ ከአርባ ምንጭና ከጅግጅጋ ከተሞች ጋር እንኳን መወዳደር የማትችልበት ደረጃ ላይ ወድቃለች።

የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት የነበሩት ምጽዋና አሰብም ባዶአቸውን ቀርተዋል። አገዛዙ ልማትንና ተቋማትን መገንባት ትቶ ሀገርን የባዕዳንና የጠላቶች መጫወቻ በማድረጉ፣ ታታሪውና ሥራ ወዳዱ የኤርትራ ሕዝብ በየበረሃውና በባህር ዳርቻዎች ለስደት፣ ለእንግልትና ለተስፋ መቁረጥ ተዳርጓል።

የኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት፣ ለፖለቲከኞችና ለሕዝቦች ትልቅ ታሪካዊ ትምህርት የሚሰጥ ነው።

ይህ የኤርትራ መራራ እውነት የመነጨው የስልጣንን እድሜ ለማራዘም ሲባል ሀገርንና ወገንን ለጠላት አሳልፎ ከመስጠት ነው።

ሌላው ደግሞ ጦርነትና የፖለቲካ ውጥረት ሀብትን የሚያወድም፤ እድገትን የሚገታ በመሆኑ፣ ከትምክህትና ከግጭት ይልቅ ትኩረትን ወደ ተቋማት ግንባታና ኢኮኖሚ ግንባታ ማዞር እንደሚገባ ያሳያል።

በተጨማሪም የአንድ ሀገር ትልቁ ሀብት ወጣቱና አምራቹ ኃይል በመሆኑ የህዝብን ስደት የሚያስቀር ሰላምና የልማት እድል መፍጠር የትኛውም መንግሥት ዋና ኃላፊነት መሆኑን እንረዳለን።

በአጠቃላይ የቀጣናው ሀገራት ከሴራና ከፖለቲካ ቁማር ወጥተው በጋራ ልማት፣ በንግድና በዘላቂ ሰላም ላይ ካላተኮሩ የጋራ ውድቀት የሚያጋጥም መሆኑን ያስገነዝበናል።

ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ከሴራና ከግጭት የጸዳ፣ በጋራ እድገትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ቀጣናዊ ትስስር እንዲፈጠር ዘወትር የምትታገለው።

ኢትዮጵያ በቅርብም ሆነ በሩቅ ከሚገኙ ጎረቤቶቿ ጋር በጋራ ለመስራት፣ የሁሉንም ወገን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመዘርጋት እና ለዘላቂ ሰላም በሩን ክፍት አድርጋ ጥሪዋን ታቀርባለች።

ምክንያቱም የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች ብሩህ መጻኢ እድል ሊረጋገጥ የሚችለው በግጭት ሳይሆን፣ በአንድነትና በጋራ ስራ ብቻ እንደሆነ ጽኑ እምነቷ ስለሆነ ነው።

Exit mobile version