አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር ትልቁ ሀብት የሰው ኃይሉ፣ በተለይም አምራቹ ወጣቱ ክፍል ነው። ወጣቱ ያለውን እውቀት፣ ጉልበትና አእምሮአዊ ብቃት ለልማት በማዋል ሀገርን የመለወጥ አቅሙ ከፍተኛ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ለትግራይ ወጣቶች ያስተላለፉት መልዕክት የትውልድን ህልውና የማዳን እና ወጣቱን ወደ ልማትና ለውጥ ኃይልነት የመመለስ ትልቅ ሀገራዊ ጥሪ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በቆታቸው ለትግራይ ወጣቶች ጥያቄ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሕገወጡ ቡድን መሪዎች ተንደላቅቀው እየኖሩ፣ ልጆቻቸውን ወደ ውጭ ሀገር ልከውና ቤተሰቦቻቸውን አዲስ አበባ አስቀምጠው በወርቅ ንግድና በህንጻ ግንባታ ላይ ሲሰማሩ፤ አንተ ለምን ትሞታለህ? ለምንስ ትቆስላለህ?” ሲሉ እያንዳንዱ የትግራይ ወጣት ራሱን ሊጠይቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
መሪዎቹ “ከደርግ ጋር ለ50 ዓመታት ተዋግተና፤” እያሉ ሳይሞቱና ሳይቆስሉ የወጣቱን ህይወት ግን ለግል ስልጣናቸው እና ሃብት ማስቀጠያነት እየተጠቀሙ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።
በመሆኑም የትግራይ ወጣት ህይወቱ የራሱ እንጂ የድርጅት አለመሆኑን ተገንዝቦ ለቤተሰቦቹ፣ ለራሱና ለክልሉ ልማት መኖር እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክራቸውን ለግሰዋል።
የትግራይ ወጣት ውሎው በጦር ሜዳ ሳይሆን በዩኒቨርስቲ፣ በንግድ፣ በእርሻ ሥራና በፋብሪካዎች ውስጥ ሊሆን ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወጣቱ የጠመንጃ ቃታ ከመሳብ ይልቅ ወደ ልማት መመለስ፣ አእምሮውንና አካሉን ለሀገር ግንባታ ማዋል ዋነኛ ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ሕገወጡ ቡድን ረብ የለሽ ከሆነ የጥፋት ኃይሎች ጋር ተሻርኮ የሚያመጣው ምንም አይነት አዎንታዊ ለውጥ ስለማይኖር የትግራይ ወጣት እውነታውን በመረዳት ወደ ሰላምና ልማት ሊመለስ ይገባል።
ሀገር የሚለማው በሥራና በቴክኖሎጂ ነው። የፌደራል መንግሥት ለወጣቱ የተሻለ የወደፊት ተስፋ፣ የትምህርትና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።
ስለሆነም የትግራይ ወጣቶች ሰላማዊ ህይወታቸውን በመምራት እና በሀገራቸው ብልጽግና ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን አዲስ ታሪክ መጻፍ ይገባቸዋል።
በዮናስ ጌትነት

