Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አቶ ጌታቸው ረዳ ከተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ከተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጓንግ ኮንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡

አቶ ጌታቸው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው እንዳስታወቁት÷ ውይይቱ በዋናነት በሱዳን ግጭት፣ በቀጣይ በሚደረገው የደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ምርጫ እንዲሁም በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

በዚህ ወቅት አቶ ጌታቸው በትግራይ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ለልዩ መልዕክተኛው ገለፃ ያደረጉ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት አዲስ ለተቋቋመው የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ድጋፍ ማድረግ በሚችልበት ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በትግራይ የመልሶ ማቋቋም ጥረቶችን ለማጠናከር፣ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን ለማፋጠን እና ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም የአስመራው አገዛዝ ቀጣናውን በተለይም ኢትዮጵያ የብሔራዊ ደህንነት እና ሉዓላዊነት ስጋት ውስጥ እንድትገባ እያደረገ ያለውን አጥፊ እንቅስቃሴ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገንዘብ ለልዩ መልዕክተኛው ማብራሪያ ሰጥቻለሁ ብለዋል፡፡

አምባሳደር ኮንግ በበኩላቸው፣ ተቋማቸው በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ትርጉም ያለው ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

Exit mobile version