አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የወደሙ መሰረተ ልማቶችን የመጠገንና ለአገልግሎት እንዲበቁ የማድረግ ሥራ እንሰራለን አሉ የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሽሻይ አማረ (ዶ/ር)።
ከመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ጋር የተወያዩት ሽሻይ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት÷ በቀጣይ 6 ወራት የሚቆየው የባለአደራ አስተዳደሩ ተልዕኮ ዋነኛ ትኩረት የሕዝቡን አስቸኳይ ፍላጎቶች ማሟላት፣ ሰላምና ጸጥታን ማረጋገጥ እንዲሁም ለቀጣይ ምርጫ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር መሆኑን አስረድተዋል።
ከረጅም ጊዜ የግጭት ተጽዕኖ በኋላ የክልሉ ነዋሪዎች አስቸኳይ የምግብና የሕክምና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የገለጹት ከንቲባው በተለይም የድርቅ ተጽዕኖ በመኖሩ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቱ አስቸኳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የትግራይ ክልል ተማሪዎች በዚህ የትምህርት ዘመን ወደ ትምህርት ቤት እንዳልገቡ ጠቅሰው ትምህርትን በፍጥነት ማስጀመርና የገበያ እንቅስቃሴን ማነቃቃት የሚጠበቅባቸው ተግባራት መሆናቸውን አመልክተዋል።
ነጋዴዎች ወደ መደበኛ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲመለሱና አስፈላጊ የፍጆታ ምርቶች ወደ ክልሉ እንዲገቡም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የሕዝቡን ደኅንነት ማረጋገጥ ለሌሎቹ ተግባራት መሳካት ወሳኝ መሆኑን ያስገነዘቡት ከምቲባው የጸጥታ አካላትና የፌዴራል ፖሊስ የሰላምና ጸጥታ ማረጋገጥ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሕዝቡም ከመንግሥትና ከባለአደራ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ለሰላምና ጸጥታ መረጋገጥ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በየአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ለሕዝብ ደኅንነት ስጋት የሚሆኑ ጉዳዮችን ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅና በሰላም ግንባታ ሥራዎች በመሳተፍ የባለአደራ አስተዳደሩን ተልዕኮ ሊያግዙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከዚህ ባሻገር በግጭት ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን፣ ጤና ጣቢያዎችንና የመንግሥት ተቋማትን መልሶ የማቋቋም ሥራ እንደሚከናወን ገልጸው የልማት መሠረተ ልማቶችን ማገገም የሕዝቡን መደበኛ ኑሮ ለማስመለስና የአገልግሎት አቅርቦትን ለማሻሻል ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።
የመቐለ ከተማን የኮሪደር ልማት በተመለከተም ሥራው ከተማዋን ከማልማት ባሻገር የክልሉን ሌሎች ከተሞች ልማት ለማበረታታት እንደሚያግዝ አንስተው የኮሪደር ልማቱ ከመጀመሩ በፊት የሕዝብ ምክክር እንደሚደረግና የነዋሪዎች ጥያቄዎችን በመለየት ተገቢ መፍትሔ ለመስጠት እንደሚሠራ አስረድተዋል።
የባለአደራ አስተዳደሩ ሥልጣን በሕግ በተወሰኑ ተግባራት ላይ የተገደበ እንደሆነ እና የመሬት ዝውውር፣ የማዕድንና የኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥ እንዲሁም ሰፊ ሕጋዊ ውሳኔዎችን ማሳለፍ ከተሰጠው ሥልጣን ውጭ እንደሆኑ ገልጸዋል።
የባለአደራ አስተዳደሩ የስድስት ወራት ተልዕኮ ውጤታማ እንዲሆን የሕዝቡ ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ያመለከቱት ከንቲባው ለሕዝቡ የተረጋጋ አካባቢ በመፍጠር የተመረጠ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ የሚያስፈልጉ ተግባራትን ለማሳካት በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የትግራይ ክልልን ለሚቀጥሉት 6 ወራት የሚያስተዳድረው ባለአደራ አስተዳደር በአቶ አሰፋ አብርሃ ሐጎስ፣ ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር)፣ ብሪጋዴር ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር በየነ፣ አቶ ረዳኢ ኃለፎም እና ሽሻይ አማረ (ዶ/ር) የሚመራ ዋና አስፈጻሚ ካቢኔ ተሰይሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል።
በዮናስ ጌትነት

