Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጉባ ብስራቶች ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ መሰረት የሚጥሉ አስተማማኝ ተቋማዊ ቁመናና አቅጣጫ ይዘዋል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የጉባ ብስራቶች ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት የሚጥሉ አስተማማኝ ተቋማዊ ቁመናና አቅጣጫ ይዘዋል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽንን በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የጉባ ብስራቶች የኒውክሊየር ሃይል ማመንጫ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ፣ የነዳጅ ማጣሪያና የቤቶች ልማት ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን መመረቅ ይፋ ካደረጉ በኋላ፤ በቀጣይ ጥቂት ዓመታት በሰላሳ ቢሊየን ዶላር የሚገነቡ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ማብሰራቸው ይታወሳል፡፡
በጉባ ብስራቶች ከተበሰሩ ትውልድ አሻጋሪ ፕሮጀክቶች መካከል የኒውክለር ኃይል ማመንጫ አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉም ፕሮጀክቶች በአስደማሚ ፍጥነት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፍያ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ከአራት ወር ባነሰ ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ገልጸው፤ ሁለተኛው ዙር ተከትሎ ይጀመራል ብለዋል።
የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ የመጀመሪያው ዙር ተመርቆ ሁለተኛው ተጀምሯል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በአስተማማኝ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
የማዳበሪያ ፋብሪካውን ከተፈጥሮ ጋዝ ጋር የሚያስተሳስር መስመር መዘርጋቱን ገልጸው፤ አሁን ደግሞ ከወደብ ጋር የሚያገናኝ ማስተላለፊያ መስመር ጀምረናል ነው ያሉት፡፡
የቤቶች ግንባታን እውን ለማድረግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየገቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሞርጌጅ ባንክ ለመፍጠር ጥናት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር እንደመሆኗ በኒውክሊየር ቴክኖሎጂ የዘገየች ቢሆንም አሁን ላይ ያለችበት ቁመና የሚያኮራ መሆኑን ገልጸዋል።
በኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ወረቀት ላይ ያለውን በሚታይና በሚጨበጥ ሁኔታ ፕሮጀክት መሥራት የሚያስችል ቁመና ተፈጥሯል ብለዋል።
አባቶቻችን በአንድ ክረምት አርሰው ያገኙትን ሁሉንም ከመብላት ይልቅ ለክፉ ቀን ብለው ይቆጥባሉ፤ ይህ የኢትዮጵያውያን ባህል ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
እኛም ያገኘነውን ሀብት እንደ ኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ባሉ ለትውልድ ተሻጋሪ መሰረተ ልማቶች ግንባታ በማዋል የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን እናደርጋለን ብለዋል።
ኒውክሊየር ቴክኖሎጂ በግብርና በምግብ ራስን ለመቻል፣ በጤናው ዘርፍ ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር፣ ኢንዱስትሪዎችን የሚያንቀሳቅስ የማይዋዥቅ ሀይል ለማቅረብ እና የሰው ሀይል አቅምን ለማጎልበት ወሳኝ በመሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ኢነርጂ የምታመርትና የምትሸጥ፣ ኢንዱስትሪዎችን የምትስብ፣ የመንገድ፣ ባቡርና የቤት መሰረተ ልማት መገንባት የምትችል መሆን አለባት ነው ያሉት።
የተገነባውን መሰረተ ልማት ማስተዳደር የሚችል ተቋም መገንባት የሚችል አቅም መፍጠር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
Exit mobile version