አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በታሪክ ማህደር ውስጥ የታላላቅ ሀገራት እድገት ቀጣይነት ምሥጢር የዛሬውን ብቻ ሳይሆን፤ የነገውን ትውልድ አርቆ ማየት መቻላቸውና በዚያው አግባብ መሰረት መጣላቸው ነው።
ኃይል የኢኮኖሚ እድገት የጀርባ አጥንት ነው። በቂና አስተማማኝ የኃይል አማራጭ የሌላቸው ሀገራት ፈጣንና ዘላቂ እድገትን ማረጋገጥ አይችሉም።
ዛሬ በዓለማችን የኃይል ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመጣበትና የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት በደቀነበት ወቅት ሀገራት ዘላቂና ንጹህ የኃይል አማራጮችን ለማስፋፋት የሚያደርጉትን ጥረት አፋጥነዋል።
ኢትዮጵያም ይህንን ዓለም አቀፋዊ እውነታ በመረዳት የላቀ ቴክኖሎጂና የዘመናዊነት ከፍታን ለመቆናጠጥ የሚያስችላትን የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ልማት መንገድን ምርጫዋ አድርጋለች።
የኃይል ምንጮቿን አማራጭ ለማስፋት የኒውክሊየር ቴክኖሎጂን መምረጧ ጊዜውንና የእድገት ፍጥነቷን ከግምት ያስገባ ውሳኔ ነው።
ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከጉባ ምድር የተበሰረው ይህ የምስራች ኢትዮጵያ ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ፣ የኃይልና የኢኮኖሚ ልዕልና ለመሸጋገር የያዘችውን ፅኑ አቋም የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት መበሰር የኃይል አቅምን በዘላቂነት ለማሳደግ የተወጠነ አዲስ ታሪካዊ ርምጃ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽንን በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት÷ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ በአንድ ዘርፍ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን፤ ለሀገር ሁለንተናዊ የልማት ጉዞ ግብዓት የሚሆን መሰረታዊ የእውቀት ምንጭ ነው።
የዚህ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ከተራ ፕሮጀክቶች በላቀ መልኩ ከ60 እስከ 100 ዓመታት የሚዘልቅ ትጋትን የሚጠይቅ፣ የአንድን ትውልድ እድሜ ተሻግሮ ለብዙ ትውልዶች የብልጽግና ትሩፋት የሚያፈራ የረጅም ጊዜ መሰረት ነው።
የኒውክሊየር ኃይል አማራጭ ምንም ዓይነት የካርቦን ወይም የግሪንሃውስ ጋዝ ልቀት ስጋትን አያመጣም። ይህም እንደ ከሰልና ነዳጅ የመሳሰሉትን የኃይል አማራጮች ከመጠቀም የሚመጣውን የከባቢ አየር ብክለት በመቀነስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመታገልና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።
ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉባ ላይ ይህንን ውጥን ይፋ ካደረገችበት ጊዜ ጀምሮ በጥናትና በሕጋዊ ማዕቀፍ የተደገፈ ተቋማዊ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታ እነሆ ስራውን አሐዱ ብላ ጀምራለች።
አሁን ላይ ሀገሪቷ በሁለት ክፍሎች በድምሩ 2 ሺህ 400 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫን ለመስራት አቅዳለች። ይህ ፕሮጀክት ከኃይል ማመንጨት ባለፈ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው።
ለጤናው ዘርፍ፤ በካንሰር ህክምና ውስጥ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ የሚጫወተው ሚና የጎላ በመሆኑ የዜጎችን ህይወት ለመታደግ፣ ጤናማ ትውልድን ለማፍራት ብሎም የህክምና አገልግሎቱን ለማዘመን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
ለግብርናው ዘርፍ፤ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ምርትን ከብልሽት ለመጠበቅና ሀገራችን በምግብ ራስን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት በማፋጠን ረገድም ጉልህ ሚና ያበረክታል።
ሀገርን በጽኑ መሰረት ላይ መገንባት የዛሬን ችግር በመፍታት ብቻ ሳይሆን የነገውን ትውልድ መጻኢ እድል ቀድሞ በማሰናዳት የሚረጋገጥ ነው።
የኒውክሊየር ኃይል ልማት ለኢትዮጵያ ንጹህና አስተማማኝ ኃይልን ብቻ ሳይሆን የላቀ የህክምና፣ የግብርና እና የቴክኖሎጂ አቅምን ይዞ ይመጣል። ይህ ዛሬ የሚጣለው መሰረት ዓመታትን ተሻግሮ የነገዋን ኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ በብርሃን የሚያደምቅ ዘላቂ ዐሻራ ነው።
በመልካም ፈቃዱ

