አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ክልልን ሕዝብ ሰላምና ልማትን የሚያደናቅፍ አስተሳሰብ ከስሩ መነቀል አለበት አሉ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የጸጥታና ሰላም ጉዳዮች ዋና አስፈጻሚ ብርጋዴር ጄነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ ።
የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር አስፈጻሚዎች ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ጋር የውይይት መድረክ አካሂደዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር በየነ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይት በመፍታት ወደ ግጭት የሚያመሩ መንገዶች መዝጋት ያስፈልጋል።
ለትግራይ ወጣቶች ልማትን እንጂ ግጭት አናወርሳቸውም ያሉት ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር÷ የትግራይ ወጣት ሰላምን በማስጠበቅ ወደ ልማት በመግባት ድህነትን መዋጋት አለበት ብለዋል።
ሕዝባዊ ውይይቱም የትግራይ ወጣት በሕገ-ወጡ የሕወኅት ቡድን ያሳለፈውን ስቃይ እና ውድመት እንዲያጤን በማድረግ በአዲስ መንፈስ በሰላምና ልማት ግንባታ ለማካካስ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅበት ለማሳወቅ መሆኑን አመልክተዋል።
በክልሉ ማናቸውም ፖለቲካዊ ልዩነቶችና ጥያቄዎች በሰከነና ስልጡን በሆነ ውይይት፣ የሕዝብን ፍላጎት ባማከለ መንገድ መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።
የትግራይ ሕዝብ ከእንግዲህ ጭቆናን የሚሸከም ጫንቃ የለውም ፤የሕዝብን ጉስቁልና በማባባስ ሰላምና ልማትን የሚያደናቅፍ አስተሳሰብ ከስሩ መነቀል አለበት ብለዋል።
በሕገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን ምክንያት በትግራይ ክልል የተቋረጡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ሕዝቡ የሰላምና ደኅንነት ዘብ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
የትግራይ ባለአደራ አስተዳደር የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ ጉዳዮች ዋና አስፈጻሚ ዶ/ር ቴዎድሮስ አረጋይ በበኩላቸው÷ የትግራይ ክልል ሕዝብ የተጎናጸፈውን ወርቃማ ዕድል ሰላምና ልማትን በማስቀጠል መጠቀም አለበት ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተፈጠረውን ዕድል በመጠቀም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የመልሶ ግንባታ ተግባራትን ለማከናወን በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ለዚህም በትግራይ ክልል ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በማቃለል የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሕዝባችን ጋር በመተባበር ተቀናጅተን ለመሥራት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

