አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ዘርፉን ሁለንተናዊ ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ አዳዲስና ዘመናዊ አሠራሮችን መተግበር ይገባል አሉ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር)።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ በክላስተር ልማት የተመዘገቡ ውጤቶችና በዳኜ ዳባ የግብርና ኢንቨስትመንት የተከናወኑ ሥራዎች ላይ ምልከታ ተደርጓል።
በጉብኝቱ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩርን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ተሳትፈዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በግብርና ዘርፍ እየተሠራ የሚገኘው ሥራ ለሌሎች ክልሎች ተሞክሮ የሚሆን ነው።
በክልሉ አዳዲስ የግብርና አሠራሮችን በመተግበር በተለያዩ ዘርፎች የተከናወነው ሥራ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
በተለይም አዳዲስና ያልተለመዱ ሰብሎች፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ተልባ እና ሌሎች በርካታ ምርቶች እየተመረቱ መሆኑን ጠቁመው÷ የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።
አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው÷ የበጋ መስኖን ማስፋፋት፣ የክረምት ምርትን በተቀናጀ አሠራር መሰብሰብና የድህረ ምርት ብክነትን መቀነስ የዘንድሮው የግብርና ዘርፍ ቁልፍ ትኩረቶች ናቸው ብለዋል።
ክልሉ የበጋ ወቅት የግብርና ልማትን በተቀናጀ ንቅናቄ በማከናወን ከ149 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማትና 38 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅዷል ነው ያሉት።
የሚከናወነው ሥራም ያሉትን የውሃ ሀብቶች በሙሉ በመጠቀም የመሬትን ምርታማነት ከፍ ለማድረግና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ እንደሆነ አስረድተዋል።
በተለመደው የምርት ወቅት ብቻ ሳይወሰኑ፣ የአፈር እርጥበትና የውሃ አማራጮች ያሉባቸውን መሬቶች በማልማት የበቆሎና ሌሎች ሰብሎችን ምርት ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በክልሉ በዘንድሮው የመኸር እርሻ 830 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ71 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት የሚጠበቅ መሆኑንም የክልሉ ግብርና ቢሮ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

