አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል የተቋቋመው የባለአደራ አስተዳደር የሕዝብ አገልግሎቶችን ለማስጀመር እና ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችን አጠናቆ ወደ ተግባር ገብቷል አሉ የአስተዳደርና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈጻሚ አቶ አሰፋ አብርሃ።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች በዛሬው ዕለት ከመቐለ ከተማ መምህራን እና ከትምህርት ቤት አስተዳደር አካላት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ውይይቱን አስመልክቶ አቶ አሰፋ እንደገለጹት÷ ሕገወጡ ቡድን በሁለት ሳምንት ውስጥ አዲስ አበባን ተቆጣጥሬ መንግሥትን አፈርሳለሁ በሚል እብሪት የጀመረው ጦርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሸንፎ ከሀገር ሁሉ ተጠራርጎ ወጥቷል።
አሁን ላይ በትግራይ ክልል ሰላም መውረዱን የጠቆሙት ዋና አስፈጻሚው ባለአደራ አስተዳደሩ ቅድሚያ የሰጣቸውን የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ለማስጀመር እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስጀመር ዝግጅቶች መደረጋቸውን እና መቐለን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች ትምህርት ለማስጀመር የሚደረጉ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆኑን ጠቁመዋል።
በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ሕዝቡ የራሱን ከንቲባና አስተዳዳሪዎች በቀጥታ እንዲመርጥ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው የአስተዳደር ኮሚቴዎች ከተደራጁ በኋላ የፖሊስና ሚሊሻ አደረጃጀቶችን በማጠናከር የአካባቢው ጸጥታ ሙሉ በሙሉ እንዲረጋገጥ ይደረጋል ብለዋል።
በክልሉ በድርቅ ምክንያት በተፈናቃዮች ላይ የደረሰውን ችግር ለመቅረፍ ከፌደራል መንግሥት፣ ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተቀናጀ የእርዳታ ሥርጭት ሥርዓት እንደሚዘረጋም አመልክተዋል።
ባለአደራ አስተዳደሩ በቀጣይም የጤና፣ የግብርና፣ የሲቪል ሰርቪስና የንግድ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ በማድረግ ሕዝቡ የልማቱ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን ይሰራል ብለዋል።
በዮናስ ጌትነት

