አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የክልሉን እምቅ አቅም ወደ ሀብት በመቀየር የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል ይጠበቅብናል አሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፡፡
በክልሉ “ጊዜ የለንም፤ ከሹመት ወደ አገልግሎት፣ ከዕቅድ ወደ ተግባር፣ ከተግባር ወደ ውጤት” በሚል መሪ ሐሳብ የመጀመሪያው የመደመር መንግሥት ስብሰባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የስብሰባው ዋና ዓላማ አዲስ የአመራር ባሕል፣ የሥራ መንፈስ፣ የአፈጻጸም ሥርዓትና የውጤት ታሪክ ማስጀመር ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየተተገበረ ባለው የለውጥ ሂደት በሕዝቡ ዘንድ አዲስ ተስፋ መፈጠሩን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ተስፋ በተጨባጭ ውጤት ማረጋገጥና ለሕዝቡ ማሳየት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመሆኑም ከእያንዳንዱ አመራር የሚጠበቀው የሪፖርት ብዛት ሳይሆን የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል የሚመዘን ተጨባጭ ውጤት ነው ብለዋል፡፡
በሕዝቡ ዘንድ ከመንግሥት ምላሽ የሚጠብቁ በርካታ የተከማቹ ጥያቄዎች እንዳሉ ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ እነዚህን ጥያቄዎች በቅደም ተከተል ለይቶ ከሀብትና ከአቅም ጋር በማጣጣም መመለስ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
እነኝህን ሥራዎች ለመስራት ክልል በተፈጥሮ ሀብት፣ በማዕድን፣ በሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች እና መስራት በሚችል የወጣት ጉልበት የታደለ በመሆኑ እነኝህን ሀብቶች ተጠቅሞ የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ ሥራዎችን ማከናዎን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በአበበች ኬሻሞ

