አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) 12ኛውን የጣና ፎረም ዓለም አቀፍ ጉባኤ አስመልክቶ በባህር ዳር ከተማ ለትራፊክ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችና አማራጭ የትራፊክ መስመሮች ይፋ ተደርገዋል።
ጥቅምት 14 እና 15 ቀን 2019 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ የሚካሄደውን ጉባኤ ተከትሎ የክብር እንግዶችን አቀባበልና ሽኝት በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማከናወን ከአየር ማረፊያው እስከ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አደባባይ የሚዘልቀው ዋና መንገድ ለተሽከርካሪዎች ዝግ እንደሚሆን የከተማው ፖሊስ መምሪያ አሳውቋል።
የፖሊስ መምሪያው አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ እንዳሉት÷ የከተማዋ ነዋሪዎችና ሌሎች የመንገድ ተጠቃሚዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው እንዳይስተጓጎልና የትራፊክ ፍሰቱ ያለ መደናቀፍ እንዲቀጥል የሚከተሉትን አማራጭ መንገዶች እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል፦
ከአባይ ማዶ ለሚመጡ አሽከርካሪዎች፦ በአሮጌው ድልድይ አድርገው በሚመጡበት ወቅት የአልማ ወተር ፍሮንት መስመርን መጠቀም ይችላሉ።
ከመሀል ከተማ ወደ ገጠር መንገድ ለሚንቀሳቀሱ፦ በአዝዋ አድርገው ወደ ሙሉ ዓለም፣ በሰርፀ ጀርባ ቀጥታ ወደ 6ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ በሚያስወጣው ዋና የኮብልስቶን መንገድ በማለፍ፣ የድሮውን አልካን አቋርጠው ወደ ሀይሌ ትምህርት ቤት እና ቀጥታ ወደ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን መጓዝ ይችላሉ።
ከገጠር መንገድ ተነስተው ወደ ከተማ ለሚገቡ፦ በጎፋ ካቶሊክ ሆስፒታል በኩል አድርገው ዲፖን በመቁረጥ ወደ ኪዳነ ምህረት መስመር መጠቀም የሚችሉ ይሆናል።
በኤርፖርት መስመር ለሚንቀሳቀሱ፦ ዋናውን የተባበሩት እና ሰራፂዮን ማርያም መስመርን በመጠቀም በኢላ ማደያ አድርጎ በማርዳ እብነ-በረድ 40 ሜትር አስፓልት ወደ ዋናው መስመር መግባት ይቻላል።
በተጨማሪም የኤርፖርት ታክሲዎች ጊዜያዊ ማቆሚያ (ፌርማታ) ለፓርኪንግ ተብሎ በተዘጋጀው በአልማ ወተር ፍሮንት መንገድ ላይ የተዘጋጀ መሆኑን የፖሊስ መምሪያ አዛዡ መጠቆማቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል።
በሌላ በኩል ጉባኤው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ባሉት ቀናት በጣና ሐይቅ ላይ ምንም አይነት የጀልባ እንቅስቃሴ የማይኖር በመሆኑ የወደብ አካባቢ ማህበረሰብ፣ የጀልባ አሽከርካሪዎችና ተገልጋዮች አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

