Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

መገጭ በሀገሬ ተጀምሮ ለዓመታት የተተወውን የፕዋሉጉን ፕሮጀክት እንደገና እንዳስጀምር አነሳስቶኛል – የጋና ፕሬዚደንት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመገጭ ፕሮጀክት ወደ ሀገሬ ተመልሼ ተጀምሮ ለዓመታት የተተወውን የፕዋሉጉን ፕሮጀክት እንደገና እንድቀሰቅስ አነሳስቶኛል አሉ የጋና ፕሬዚደንት ጆን ድራማኒ ማሃማ።
የጋናው ፕሬዚደንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በመሆን ታሪካዊቷን የጎንደር ከተማ በጎበኙበት እና የመገጭ ፕሮጀክትን በይፋ ባስመረቁበት ወቅት እንዳሉት÷ የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአመራር አስደናቂ ነው።
የመገጭ ፕሮጀክት ለዓመታት ተጓትቶ ከሦስት ዓመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አነሣሽነት አዲስ ሕይወት ዘርቶ ለምረቃ መብቃቱን አንስተው ይህም በጋና ለዓመታት ተጀምሮ የቆየውን የ‘ፕዋሉጉ’ የመስኖ እና የኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ እንዲያስጀምሩ እንዳነሣሣቸው ተናግረዋል።
በጋና ከብዙ ዓመታት በፊት የተጀመረ ነገር ግን የተተወ ተመሳሳይ ግድብ አለን ያሉት ፕሬዚደንቱ ወደ ሀገሬ ተመልሼ የመስኖ ፕሮጀክትን እንደገና እንዳስጀምር አነሳስቶኛል ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እና የጋና ታሪካዊ ትሥሥር ለዓመታት የዘለቀ መሆኑን አንስተው ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት መሆኗን እና ጋናም ከሰሐራ በታች ካሉ ሀገራት ነፃነቷን በማወጅ ቀዳሚ መሆኗን ጠቅሰዋል።
በተለይም የጎንደር ስም በጋና ልዩ ቦታ እንዳለው በመግለጽ በሀገራቸው ዋና ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ‘ጎንደር ባራክስ’ (የጎንደር የጦር ሰፈር) የሚባል ስፍራ መኖሩን እና ይህም በታኅሣሥ 31ዱ የጋና አብዮት ወቅት ዋና መምሪያ እንደነበር አስረድተዋል።
የቀደሙት የአፍሪካ መሪዎች አህጉሪቱን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት መታገላቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ማሃማ የዛሬዎቹ መሪዎች ዋነኛ ኃላፊነት ደግሞ ለሕዝባቸው ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን እና ብልጽግናን ማምጣት መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።
Exit mobile version