አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የምሥራቅ አፍሪካን የማያቋርጥ የጽንፈኝነትና ሽብርተኝነት ስጋት በመቀልበስ የቀይ ባሕርን ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናው ሀገራትን ትብብር ማጎልበት ይገባል አሉ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን።
12ኛው የጣና ፎረም በባሕርዳር ጣና ሐይቅ ዳርቻ “በአፍሪካ የሰላም መንገዶች የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦ-ፖለቲካ ለውጥ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው፡፡
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ አሁን ላይ የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ-ፖለቲካና ውስብስብነት እየተባባሰ መጥቷል።
የአፍሪካ ቀንድ በነዳጅ፣ ወሳኝ ማዕድናት፣ ያልታረሰ መሬትና ውሃን ጨምሮ ያልተነኩ የተፈጥሮ ሀብቶች ያሉበት ቀጣና መሆኑን ገልጸዋል።
ቀጣናው ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች የሆኑት የቀይ ባሕር፣ የሕንድ ውቅያኖስና የሜዲትራኒያን ባሕርን የሚያገናኙበት ስትራቴጂክና ወሳኝ መስመር መሆኑንም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ ታሪካዊ በደሎች፣ የሀብት ውዝግብና ውስብስብ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ውጥረቶች ያሉበት መሆኑን አስረድተዋል።
በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናም ጽንፈኝነትና ሽብርተኝነት የማያቋርጥ ስጋት መፍጠራቸውን ጠቁመው÷በዚህ ውስብስብ ቀጣናም በቀይ ባሕር ላይ እየጨመረ የመጣው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለቀጣናው ሀገራት ስጋት መሆኑን ገልጸዋል።
በባብኤል መንደብና በሰፊው ቀይ ባሕር ውስጥ በንግድ መርከቦች ላይ እንደ አዲስ የተከፈቱ ጥቃቶች አሉ፤ እነዚህ ክስተቶች በደጃፋችን ላይ የሚከናወኑ ለውጦች ናቸው ብለዋል።
እነዚህ ክስተቶች የቀይ ባሕር ደኅንነት በጥቂት የባሕር ዳርቻ ሀገራት ጥበቃና ባለቤትነት ላይ ብቻ ሊተው እንደማይችል ማሳያዎች መሆናቸውን ነው ያስገነዘቡት፡፡
በመሆኑም የቀጣናውን ደኅንነትና መረጋጋት ለማስጠበቅና የወደፊቱን ለመቅረጽ የቀይ ባሕር ዳርቻ ሀገራት ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ሀገራት መካከል በአስተማማኝ አጋርነትና ትብብር መፍጠር ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ የባሕር ንግድ ሙሉ በሙሉ በቀይ ባሕር የተመረኮዘና የቀጣናው መሠረት መሆኗን ጠቅሰው÷ የደኅንነት ስጋቷን የማስወገድ፣ የባሕር ንግዷንና የንግድ መርከቦቿን መጠበቅ ግዴታ እንዳለባት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስመዝገብ፣ ጠንካራ ቀጣናዊ ውህደት ለማምጣት በትኩረት እየሠራች መሆኑን አስታውቀዋል።
የቀጣናው ተለዋዋጭ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚፈጠሩትን ውስብስብ ፈተናዎች ለመሻገር ፈጠራና አካታች ስልቶችን መከተል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

