Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የወጪና ገቢ ንግድ ማዕከል የነበረችው አሰብ አሁን ባዶና ትርጉም የለሽ ሆናለች – የአሰብ የቀድሞ ም/ከንቲባ

የወጪ እና ገቢ ንግድ ማዕከል የነበረችው አሰብ ከተማ አሁን ባዶና ትርጉም የለሽ ሆናለች አሉ የአሰብ የቀድሞ ምክትል ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሊበን።

አቶ ዳንኤል ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በወቅቱ አሰብ ከስድስት የመጀመሪያ ደረጃ ከተሞች አንዷ እንደነበረች አስታውሰዋል፡፡

ባሕር ዳር፣ ጎንደር እና ሐዋሳ ዛሬ ላይ የደረሱበትን ስናይ አሰብ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደተመለሰች በግልጽ እንደሚያሳይ አብራርተዋል፡፡

አሰብ ከተማ የወደብ ሥራ፣ የባሕር ትራንስፖርት ቢሮዎች፣ ባንኮች፣ የትራንዚት፣ የኤክስፖርት እና ኢምፖርት ድርጅቶች መናኸሪያ እንደነበረች አስረድተዋል፡፡

በከተማዋ የነበረው ከፍተኛ የሥራ እድል ከየአቅጣጫው ሕዝብን በመሳብ ለበርካታ ዜጎች ሁለተኛ ቤት እንደነበረች ነው ያወሳሉ፡፡

በከተማዋ የተገነባው የነዳጅ ማጣሪያ በምሥራቅ አፍሪካ አቻ ያልተገኘለት ትልቅ መሠረተ ልማት እንደነበርና ለበርካታ ዜጎች ከፍተኛ የሥራ እድል ፈጥሮ እንደነበርም ጠቅሰዋል።

በወቅቱ የወጪ እና ገቢ ንግድ መነኸሪያ የነበረችው አሰብ ዛሬ ላይ ያለችበት ሁኔታ ጭር ያለ እና ሰው የማይታይበት መሆኗን ተናግረዋል።

በተለይም በከተማዋ የነበሩ በርካታ ሃብትና ንብረት ያፈሩ ኢትዮጵያውያን መፈናቀላቸውን፣ አንዳንዶቹ ወዴት እንደደረሱ እስካሁን እንደማይታወቁና ቀደም ሲል በኢኮኖሚ አቅማቸው ጠንካራ የነበሩ ዜጎች ለከፍተኛ መጎሳቆል መዳረጋቸውን በቁጭት ያስታውሳሉ፡፡

አቶ ዳንኤል ሊበን እንደሚያስረዱት÷ የባሕር በር ጉዳይ በጊዜ ሒደት የሚቀያየሩ የመንግሥታት ጉዳይ ሳይሆን የሀገር ሕልውናና የትውልድ ዋስትና ነው።

ከአክሱም ስልጣኔ ጀምሮ አፄ ዮሐንስ፣ ራስ አሉላ አባ ነጋና ሌሎች የቀይ ባሕርን ወሰን ለማስጠበቅ መስዋዕትነት መክፈላቸውን በማንሳት የቀይ ባሕር አካባቢ ለቀጣናው ከፍተኛ የኢኮኖሚና የደህንነት ጥቅም ያለው መሆኑ አብራርተዋል፡፡

የባሕር በር ጉዳይን በስምምነትና በሰላማዊ መንገድ የማስከበሩን ሒደት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመቆም ሊደግፈው እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version