Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአባት ውርስ ከሃዲዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)ታሪክ ታላቅ ዐሻራውን ጥሎ ያለፈበት፣ የድንጋይ ንብርብሮች የሚናገሩበት፣ የትናንት ታሪካቸውንም የሚዘክሩበት ምድር፣ የሥልጣኔ መነሻና የቤተ እምነቶች መክተሚያ ጭምር ነው የትግራይ ምድር።
ኢትዮጵያዊነት ያለ አክሱም ሥልጣኔ ሙሉ አይሆንም። ክርስትና እና እስልምና ወደ ሀገሪቱ የገቡበት፣ አበው ጥበብን ያበለጸጉበት ይህ ምድር፣ የኢትዮጵያዊነት እና ባህላዊ መሠረት ተደርጎ ሊታይ የሚችል ነው።
ከወዲህ ደግሞ የሀገር ሉዓላዊነት አደጋ ላይ በወደቀ ጊዜ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በመሆን ጋሻና መከታ ሆኖ ቆሟል። በዓድዋ እና በሌሎች የጦር ግንባሮች የተከፈለው መስዋዕትነት የኢትዮጵያን ነፃነት በማስከበር ረገድ ዘላለማዊ ዐሻራን አኑሯል።
የኢትዮጵያ ታሪክ በብዙ ጀግኖች ደም የተጻፈ ነው። ሁሉም ስለሀገር ክብር ስለዳር ድንበሯ ዋጋ ከፍለዋል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት እስከ መጨረሻዋ የደም ጠብታ ድረስ የተዋጉ ንጉሥ አፄ ዮሐንስ አራተኛ ደማቅ ታሪክ አላቸው።
እሳቸው የሀገር አንድነት የሚፀናው በመከባበርና በመደጋገፍ እንደሆነ ከአለት የጠነከረ ዕምነት ያላቸው መሪ እንደነበሩ ድርሳናቸው ያወሳል።
በወቅቱ በየአከባቢው የነበሩ ገዢዎችን በማስተባበር፣ የውስጥ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ለኢትዮጵያዊ ልዕልና ጥረዋል፣ ደክመዋል። የታሪክ ማህደራቸውም ሲገለጥ ይህን የሚያፀና ነው፡፡
ከወዲህ ደግሞ ታላቅ የጦር ባለሟል ራስ አሉላ አባነጋ ክንደ ነበልባል። የኢትዮጵያዊነት ልኩ ጠላት ድንበር አልፎ ወሰን ጥሶ በመጣ ጊዜ እምቢኝ ብሎ ክንዱን አነሳ። ያ የጦር አበጋዝ የማይጨበጭ ነበልባል ሆነባቸው።
ድብቅ ሴራቸውንም አክሽፎ ጣፋጭ ድሉን ተቀዳጀ። የኢትዮጵያንንም ልክ ለዓለም ገለጠ። ትግራይ ያበቀለቻቸው ቀደምቶች ልካቸው ኢትዮጵያዊነት ነበር። መነሻ እና መዳረሻቸው እንዲሁ። ትግራዋይነታቸው ለሀገር ዘብ፣ ክብርና ከፍታ ከመቆምም አላገዳቸውም።
ይህ ታሪክ በደማቅ ቀለሙ ያተመው እውነት በአፄ ዮሐንስ አራተኛ እና በራስ አሉላ አባነጋ ገዝፎ ቢገለጥም ዕልፎች የዚህ ፍኖት ተጋሪ ሆነው ዘልቀዋል።
ሰርክ በስማቸው የሚምለው ሕገወጡ የህወሓት ቡድን ግን ከቀደምቶቹ ለየቅል ሆኖ ዕብለትን ዕድሜ መግዣ አድርጎታል።
አባቶቹ የደሙላትን ሀገር የሸቀጥ ያህል የሚመለከተው ቡድኑ እታገልለታለሁ ለሚለው ሕዝብ በማይበጅ አካሄድ መጓዙ ግላዊ መሻቱን ትኩረት ስለማድረጉ ማሳያ የሚሆን ነው።
ይባስ ብሎ እንደ ትዕምርት በሚጠራቸው፤ በግብር ግን በማይመስላቸው ቀደምቶቹን ከወጉና ከሚዘባበቱባቸው ጋር ውል ማሰሩ የክህደት ያህል የሚቆጠር ነው።
ታሪክ ፈተናዎች አሉት፤ ነገር ግን የዘመናት ጥልቅ ትስስርን አይበጥሰውም። ትግራዋይነት እና ኢትዮጵያዊነትም እንደዚያው ነው። ህገወጡ የህወሓት ቡድን ግን የአባቶቹን ውርስ ቃል የበላ ከስንዴ መሀል የተገኘ እንክርዳድ ነው። ከሕዝቡ ለየቅል የሆነ ክፉ አረም።
በነቢዩ ይርጋለም
Exit mobile version