አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን በአምቻ እና በጋብቻ የተሳሰረ የጥቅም ቡድን እንጂ የትግራይ ህዝብ ተወካይ አይደለም አሉ የቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ/ፕ)፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ሕገ ወጡ ህወሓት ራሱን የትግራይ ህዝብ ብቸኛ ነፃ አውጭ አድርጎ ሲመለከት መቆቱን እንዲሁም የህወሓት ሕልውና የትግራይ ህዝብ ህልውና እንደሆነ ፕሮፖጋንዳ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
ነገር ግን እውነታው ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን በአምቻ እና በጋብቻ የተሳሰረ የጥቅም ቡድን እንጂ የትግራይን ሕዝብ የሚወክል አይደለም ነው ያሉት፡፡
ከመጀመሪያውም ቡድኑ የትግል መነሻ ምክንያቱ የተሳሳተ እንደነበር የገለፁት አበባው አያሌው (ረ/ፕ)÷ በተለይም አንዳንድ የማህበረሰብ ክፍሎችን እንደ ገዢ መደብ እና እንደ ጨቋኝ በመቁጠር የትግራይ ሕዝብን ሲያሳስት ነበር ብለዋል፡፡
ቡድኑ የትግል ጅማሮውን ሲያደርግ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ትብብር ያደርግ እንደነበር አስታወሰው ሕገ ወጡ ህወሓት እና ሻዕቢያ በግብፅ አጀንዳ ሰጭነት መመሰረታቸውን ገልፀዋል፡፡
ቡደኑ በተደጋጋሚ የትግል ዓላማው ትግራይን ነፃ ማውጣት ነው ቢልም በተጨባጭ ግን የትግራይ ህዝብ አስቀድሞ ነፃ የወጣ እና በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ህዝብ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
ሕገ ወጡ ህወሓት የትግራይ ሕዝብን ባስተዳደረባቸው ዘመናት ሕዝቡን ከድህነት ማውጣት አለመቻሉን፣ በተቃራኒው ግን ቡድኑ በጥቅም ተሳስሮ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀብት ሲያከማቹ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ ከአማራ እና ከአፋር ክልል እንዲሁም ከመሀል ሀገር ጋር የጠበቀ ግንኙነት እና የታሪክ ቁርኝት ቢኖረውም፣ ሕገ ወጡ ቡድን ግን የሕዝቡን ማህበራዊ ትስስር በመበጠስ እንዲገለል አድርጎታል ብለዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

