Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አፍሪካ እየተለወጠ ካለው ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ጋር መላመድ ብቻ ሳይሆን፣ ሥርዓቱን የመቅረጽም ሚና ሊኖራት ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትረ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ እየተለወጠ ካለው ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ጋር መላመድ ብቻ ሳይሆን፣ ሥርዓቱን የመቅረጽም ሚና ሊኖራት ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የሰላም መንገዶች በአፍሪካ፦ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የጂኦፖለቲካ ሽግግር” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው 12ኛው የጣና ከፍተኛ የደህንነት ፎረም ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡
ይህንን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት÷ ከድንበር ባሻገር የሚወሰኑ ውሳኔዎች በዜጎች፣ በኢኮኖሚ ዕድሎች እና በደህንነት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ ገልጸው፣ ይህንን እውነታ ሊዘነጋ እንደማይገባ አስገንዝበዋል።
እያንዳንዱን ድንገተኛ ቀውስ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባይቻል እንኳ፣ አህጉራዊ የመቋቋም አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ለአፍሪካ ሀገር በቀል መፍትሔዎችን ማዘጋጀት፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማጠናከር እና ሁለገብ ትብብርን ማሳደግን እንደሚያካትት ገልጸዋል።
አፍሪካ እየተለወጠ ካለው ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ጋር መላመድ ብቻ ሳይሆን፣ ሥርዓቱን በራሷ መንገድ የመቅረጽ ሚና ሊኖራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ቀዳሚና እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህም ዜጎችን መጠበቅ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማክበር እና ለውይይት በርን ክፍት ማድረግን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
መንግሥት ለብሔራዊ ምክክር ባለው ቁርጠኝነት፣ የሰላምን መንገድ የሚመርጡትን ሁሉ ለመቀበል ሁልጊዜም ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም የመደመር ፍልስፍና ጥንካሬዎችን እና አቅሞችን በማስተባበር እንዲሁም ከሀገር በቀል ተጨባጭ እውነታዎች የተቀዱ መፍትሔዎችን በማዘጋጀት ላይ ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም ለወደፊት ትውልድ የምናወርሳትን ዓለም በመቅረጽ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወትን፣ ጠንካራ የመቋቋም አቅም ያላት፣ ሰላማዊ እና የበለጸገች አህጉር መገንባት እንደሚቻል ገልጸዋል።
Exit mobile version