አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ቁጥሯ ከ130 ሚሊየን በላይ ለሆነችው ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የህልውና፣ የደህንነት እና የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
12ኛው የጣና ፎረም የመክፈቻ መርሐ ግብር በውቢቷ ባሕር ዳር በጣና ሐይቅ ዳርቻ “በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦፖለቲካ ለውጥ” በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ ጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፎረሙ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው÷ ለመጪው ትውልድ የሚሻገር ታላቅ ሥራ ለመሥራት ታቅዶ ወደ ዓለም የሚያመራው እያንዳንዱ መንገድ በሌሎች ሀገራት እንዲያልፍ መገደዱ የሀገርን ደህንነት፣ ሉዓላዊነት እና የልጆችን የወደፊት ተስፋ የሚመለከት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍላጎቷን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት በውይይት፣ በሰላማዊ መንገድ እና በጋራ ጥቅም መርህ ላይ የተመሠረተውን አካሄድ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
በመልካም ፈቃዱ

