አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢፌዲሪ አየር ኃይል የኢትዮጵያን የአየር ክልል በአስተማማኝ ብቃት እየጠበቀ የሚገኝ፣ የሀገር ኩራትና የሕዝብ መመኪያ ታላቅ ተቋም ሆኗል።
ባለፉት ዓመታት ተቋሙ በርካታ አስደናቂ ስኬቶችን አስመዝግቧል።
አየር ኃይሉ ከፍታውን ያረጋገጠ ቁመና ላይ የሚገኝ ቢሆን ባልተቋረጠ ሪፎርም በማለፍ የበለጠ ልቆ ለመገኘት መዘጋጀት፣ የበለጠ መማር፣ የበለጠ መሥራት፣ የበለጠ መትጋትና በሙያ ስነ ምግባር መላቅ እንዲሁም በሁሉም መስክ የላቀ ውጤት ማስመዝገብን መርሁ አድርጎ እየሰራ ነው።
በትናንቱ ድልና ስኬት ሳይዘናጋ፣ የነገውን ፈተና በማሰብ ዛሬን በትጋት በመስራት ላይ ይገኛል።
ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ለሕዝቡ ሰላምና ደህንነት፣ ለተቋሙ ክብርና ለትውልድ የሚተላለፍ አኩሪ ታሪክ በተለመደው ጀግንነት፣ በሙያዊ ብቃትና በቁርጠኝነት እየሰራ የሚገኘው አየር ኃይሉ፤ የኢትዮጵያ አስተማማኝ ዘብ ነው።
በተቋሙ ውስጥ ያሉ የጦር ክፍሎች አንድ ልብ ሆነው ለአንድ ዓላማ እየሰሩ መሆኑን የሚገልጹት የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ ይህ ትብብር የተቋም ደህንነት ዋስትና ከመሆን በላይ ለሀገር ጋሻና መከታ መሆኑን ይናገራሉ።
የሀገር መመኪያ የሆነው ተቋሙ የአካባቢውን ሰላም በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ የሚገኝ ሲሆን፤ በየጊዜው የመሪነት አቅሙን በማሳደግ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሰራዊቱን ወትሮ ዝግጁነት በማረጋገጥ ተልዕኮውን መወጣቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
አሁን የምንገኝበት ዘመን የውጊያ አካሄድና ስልት ለመገመት በሚያዳግት መልኩ በፍጥነት እየተቀያየረ መምጣቱን ታሳቢ ያደረገ ቁመና በመላበስ፤ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ከፍተኛ ለውጥ እያደረገ ከወቅቱ ጋር አብሮ እየተጓዘ ይገኛል።
አየር ኃይሉ የዘመኑን ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችል የሰው ኃይል በማብቃት በርካታ ፓይለቶችን፣ ቴክኒሽያኖችንና የአስተዳደር ባለሙያዎች እያፈራ እና የዘመኑን የውጊያ ቴክኖሎጂዎች እየታጠቀ ነው።

