Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዜጎች የምርትና አገልግሎት ጥራትን ባህል እንዲያደርጉ በቁርጠኝነት ይሰራል – መሰረት በቀለ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዜጎች የምርትና አገልግሎት ጥራትን ባህል እንዲያደርጉ በትብብር ይሰራል አሉ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ (ዶ/ር)።
ኢንስቲትዩቱ የዓለም ደረጃ ቀንን “ንጹህና አዋጭ የኃይል ምንጮችን መጠቀም” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ሁነቶች እያከበረ ነው።
መሰረት በቀለ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የምርትና አገልግሎት ጥራት እንደሚገባቸው አውስተዋል።
አሁን ላይ በሁሉም ዘርፎች ለምርትና አገልግሎት ጥራት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው÷ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ጥራትን ባህል እንዲያደርግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ አመራሮችና ሠራተኞች በዓሉን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በዚህ ወቅትም ዓለም አቀፍ የሆኑት የአይ.ኤስ.ኦ እና የኢ.ኤ.ስ ደረጃዎች በአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማቶች ላይ ተተግብረው በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ከአምራቾችና አስመጪዎች እንዲሁም ከአገልግሎት ሰጪዎች ጋር ጥራትን ባህል በማድረግና በደረጃ ትግበራ ላይ ትኩረት ያደረገ ምክክር መካሄዱንም ኢንስቲትዩቱ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።
Exit mobile version