Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የከሰረው የፅምዶ ኃይል ትኩረት ለማስቀየር የብሔርና የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር ያደረገው እንቅስቃሴ ከሽፏል – አቶ ኃይሉ አዱኛ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በሰሜን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኪሳራ የደረሰበት የፅምዶ ኃይል ትኩረት ለማስቀየር የብሔርና የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር ያደረገው እንቅስቃሴ ከሽፏል አሉ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ።

ኃላፊው ይህንን ያሉት በአርሲ ሲርካ በንፁሀን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ነው።

በመግለጫቸው የጠላት ኃይል ሀገራችን እያስመዘገበች ያለውን እድገት ለማደናቀፍ እና የሀገርን ሰላምና መረጋጋት ለማናጋት የሚያደርገው እንቅስቃሴ መቼም ቢሆን አይሳካም ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገርን ጥቅም በማስከበር ታላቅ ርዕይ ያላትን ታላቅ ሀገር ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

አቶ ኃይሉ ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት ያለው የፅምዶ ኃይል የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር የውስጥ ግጭቶችን ለማስፋፋት እየተወራጨ ይገኛል ነው ያሉት።

በዚህም በሀገር ማፍረስ ተግባር ላይ የተሰማራው አሸባሪው ኃይል በአርሲ ሲርካ ወረዳ ኮሌ እና ቢርቦ ቀበሌዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ ባደረሰው የህይወትና የንብረት ጉዳት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀዋል።

ይህንን ጥፋት በፈጸሙ አካላት ላይም መንግሥት  ከህዝቡ ጋር በመሆን የጀመረውን ርምጃ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አቶ ኃይሉ አመልክተዋል።

አክለውም በሰላም እጦት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸውና ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የክልሉ መንግሥት ከህዝቡ ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

በሲፈን መኮንን

Exit mobile version