አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዛሬው ውጤት የጋራ ጥረታችን እና የትብብራችን ፍሬ ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ከአምባሳደር፣ ኢሬቻና ባምቢስ እስከ ሰላም መንገድ የሚዘልቀው የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቅቆ በዛሬው ዕለት ምርቃቱ በመከናወኑ ለሕዝብ ክፍት ተደርጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ፕሮጀክቱ ከተማዋን ለመኖር፣ ለመሥራት እና ለመዝናናት ምቹ፣ አረንጓዴ እና ውብ የማድረግ ጉዞ ዋና አካል መሆኑን ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፤ የከተማ ልማት ማለት መሠረተ ልማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን ለነዋሪዎች ንጹሕና ምቹ አካባቢን፣ የመዝናኛና የማኅበራዊ ትስስር ዕድሎችን እንዲሁም የሥራና የገቢ ምንጮችን በስፋት መፍጠርም ጭምር ነው።
በዛሬው ዕለት ለህዝብ ክፍት የሆነው ይህ ግዙፍ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የታፈኑ የወንዝ ተፋሰሶችን በመንከባከብና የተፈጥሮ ሀብትን በማልማት ወደ አዲስ የቱሪስት መዳረሻነት የለወጠ ታላቅ ሀገራዊ ስኬት ነው።
የፕሮጀክቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በከፍተኛ ደረጃ የጎለበተ መሆኑን ያመላከቱት ከንቲባዋ፣ በግንባታው ሂደት ብቻ ከ56 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
የነዋሪዎችን ደኅንነትና የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ሌላው የፕሮጀክቱ ዋና ትኩረት እንደነበር የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ ቀደም ሲል ለከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ተጋልጠው የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎችን አዲስና ምቹ ወደሆኑ መኖሪያ ቤቶች በማሸጋገር የተጠበቀ የኑሮ ሁኔታ እንዲኖራቸው መደረጉን አብራርተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለዚህ ታላቅ ውጤት ከሐሳብ ማመንጨት ጀምሮ አቅጣጫ በመስጠትና በማበረታታት ላደረጉት ድጋፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በተጨማሪም በጥናት፣ በዕቅድ፣ በግንባታና በቅንጅት ለደከሙ የከተማዋ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ አማካሪዎችና ተቋራጮች እንዲሁም ለልማቱ መሳካት በትብብርና በመተማመን ከጎን ለቆሙት የመዲናዋ ነዋሪዎች ከፍተኛ አክብሮትና ምስጋናቸውን አስተላልፈዋል።
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

