አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ከጥቅምት 13 እስከ 15 ቀን በባሕር ዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው 12ኛው ዓለም አቀፍ የጣና ፎረም በስኬት ተጠናቅቋል አለ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና መምሪያ።
የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ባወጣው መግለጫ እንዳለው÷ መርሐ ግብሩ በስኬት ተጠናቅቆ እንግዶች ወደ መጡበት እስኪመለሱ የተቀናጀ የፀጥታ ማስከበር ሥራ ተከናውኗል።
መምሪያው ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ የጥበቃ፣ የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥርና ወንጀልን አስቀድሞ የመከላከል ሥራዎችን በትኩረት ማከናወኑንም ገልጿል።
ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሌት ከቀን በሙያዊ ብቃትና በተጠናከረ ዲሲፕሊን ለሠሩት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልሉ ፖሊስና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች፣ እንዲሁም የደህንነት ተቋማት መምሪያው ምስጋና አቅርቧል።
በተጨማሪም የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎችና ወጣቶች ለአካባቢያቸው ሰላምና ደህንነት በመቆርቆር ላደረጉት ከፍተኛ ትብብር አመስግኗል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና መምሪያ በክልሉ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የጀመረውን የተቀናጀ የሕግ ማስከበርና የሕዝብ ደህንነት የማረጋገጥ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጹን የክልሉ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል።

