አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በየትኛውም ሀገር የዕድገትና የብልጽግና ታሪክ ውስጥ፣ ኃይል (ኢነርጂ) የልማት ሁሉ የጀርባ አጥንትና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው።
ህይወት ላለው ነገር ሁሉ የጸሐይ ብርሃንና አየር እንደሚያስፈልገው ሁሉ ለልማት ዘርፎች ማበብ፣ ለኢንዱስትሪዎች መንቀሳቀስ፣ ለግብርና ዘመናዊ መሆን፣ ለትምህርትና ጤና አገልግሎቶች ጥራት እንዲሁም ለዜጎች የዕለት ተዕለት ህይወት መሻሻል ተመጣጣኝና ዘላቂ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ ነው።
ኃይል የሌለበት ልማት ውሃ እንደሌለው እርሻ በመሆኑ፤ የኢነርጂ አቅምን ማሳደግ የሀገርን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚደረግ መሰረታዊ ጉዞ ሆኖ ይታያል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ጸጋዎቿ የታደለች፣ የብዙ ግዙፍ ወንዞች፣ የምድር ውስጥ እሳተ-ገሞራዊ እንቅስቃሴዎችና ወሰን የሌለው የንፋስ፣ የ13 ወር የጸሐይ ብርሃን ባለቤት ናት።
ይህ ተፈጥሯዊ ሀብት ሀገሪቷን የአፍሪካ የኢነርጂ ማዕከል የመሆን ታላቅ እቅም ሰጥቷታል።
በውሃ ኃይል ማመንጨት በኩል ያላት አቅም እጅግ ግዙፍ ሲሆን፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በሌሎችም ግድቦች አማካኝነት የሚመነጨው ኤሌክትሪክ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት ብቻ ሳይሆን፤ ለጎረቤት ሀገራት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ብሎም ቀጣናዊ በትብብር የማደግ መንፈስን በመፍጠር ረገድ ትልቅ አቅም ፈጥሯል፡፡
እንደ አፋር ክልልና ስምጥ ሸለቆ ባሉ አካባቢዎች የሚገኘው ግዙፍ የምድር ውስጥ ሙቀት (ጂኦ-ተርማል) ኃይል፣ ዓመቱን ሙሉ የማይቋረጥና አስተማማኝ የኃይል ምንጭ አቅም መሆን ይችላል፡፡
በአዳማ፣ አሸጎዳና አይሻ ያሉ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች እንዲሁም እየተስፋፉ ያሉ የጸሐይ (ሶላር) ፕሮጀክቶች የታዳሽ ኃይል አጠቃቀምን በማጎልበት የአየር ንብረት ለውጥን የሚከላከል አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።
በሶማሌ ክልልና በተለያዩ አካባቢዎች የተከማቸው የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ወደ ፊት ለሀገር ውስጥ የኃይል ፍላጎትና ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃነት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
መንግሥት ኢነርጂ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ዕድገት ያለውን ቁልፍ ሚና በመገንዘብ ለዚህ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
ባለፉት ዓመታት የኃይል ማመንጫዎችን መገንባት ብቻ ሳይሆን፤ የኃይል ማስተላለፊያና ማሰራጫ መስመሮችን በመዘርጋት ተደራሽነት ላይ በሰፊው ተሰርቷል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና የኃይል ማመንጨት ምዕራፎች በስኬት መከናወናቸው፣ የንፋስና የጂኦተርማል ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸው እና ለጎረቤት ሀገራት የሚቀርበው ኃይል ማደጉ የኢትዮጵያን የኢነርጂ ዲፕሎማሲና ኢኮኖሚያዊ ጥካሬ ማሳያ ናቸው።
የኃይል አቅምን ማሳደግ ማለት ጨለማን በብርሃን መተካት ብቻ ሳይሆን፤ የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ማፋጠን፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠርና የህዝቦችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ማለት ነው።
ኢትዮጵያ ያላትን አረንጓዴና ታዳሽ የኢነርጂ ሀብት በአግባቡ አውጥታ በመጠቀም የጀመረችውን የብልጽግናና የህዳሴ ጉዞ በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም በሙሉ አቅሟ በመገስገስ ላይ ትገኛለች።
በመልካም ፈቃዱ

