አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ልማት የሚለካው በሚገነባ መሠረተ ልማት ብቻ ሳይሆን ለሰዎች በሚሰጠው አገልግሎትና በሚፈጥረው ዕድል ጭምር ነው አሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)።
3ኛው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት መካሄድ ጀምሯል።
በመርሐ ግብሩ መክፈቻ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በተወካያቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ውሃ እና ኢነርጂ የተለያዩ የልማት አጀንዳዎች አይደሉም።
ውሃ እና ኢነርጂ የምግብ ዋስትና፣ የማህበረሰብ ጤና፣ የኢንዱስትሪ እድገት እና ብሔራዊ የመቋቋም አቅም መሠረቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ውሃ የኃይል ማመንጨት እና ምርታማ ግብርናን እውን ሲያደርግ፣ ኢነርጂ ደግሞ ውሃን ለማውጣት፣ ለማከም፣ ለማሰራጨት እና መስኖን ለማስፋፋት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
ሀገሪቱ ከፍተኛ የውሃ እና የታዳሽ ኢነርጂ አቅም፣ ወጣት ኃይል እና እያደገ የመጣ የመሠረተ ልማት ፍላጎት እንዳላት አንስተው፤ ይህም ጥንቃቄ የተሞላበት አስተዳደር እና ቁርጠኛ ርምጃ እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።
ልማት የሚለካው በሚገነባ መሠረተ ልማት ብቻ ሳይሆን ሰዎች በሚያገኟቸው አገልግሎቶች እና በሚፈጥሩት እድሎች ጭምር መሆኑ ጠቁመዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ትምህርትን፣ ጤናን፣ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን እና ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ እንዳለበት አንስተዋል።
ብቁ ተቋማት፣ ግልጽ ኃላፊነቶች፣ ዘላቂ ፋይናንስ እና ውጤታማ ቁጥጥር አስፈላጊ መሆናቸውን ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) አስምረውበታል።
አንድ ተቋም የውሃ እና ኢነርጂ ደህንነትን ብቻውን ማቅረብ እንደማይችል በመግለጽ፤ የተቀናጀ አሰራር አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
የመደመር መንግሥት አመራር በመስጠት፣ ዩኒቨርሲቲዎች ምርምር በማጋራት፣ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት በማምጣት እና ማህበረሰቡ እንደ አጋር በመሳተፍ በውሃ፣ በኢነርጂ፣ በምግብ እና በሥነ-ምህዳር መካከል ያለውን ትስስር አቀናጅቶ ሊጓዝ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመልካም ፈቃዱ

