Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዴንማርክ በኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ያላትን ድጋፍ ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት – አምባሳደር ሱኔ ክሮግስትሩፕ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዴንማርክ በኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ያላትን ድጋፍ ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት አሉ በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሱን ክሮግስትረፕ።
3ኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት “ለውሃና ኢነርጂ ዋስትና የተጠበቀለት የወደፊት ሁኔታ ሳይንሳዊ መሠረት ያላቸውን ፖሊሲዎችና አጋርነቶችን ማሳደግ” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሱን ክሮግስትረፕ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ዕውቀትን ለመለዋወጥ፣ ልምድን ለመካፈል፣ የፈጠራ ሥራዎችን ለማስተዋወቅና ትብብርን ለማጠናከር እያገለገለ የሚገኝ መድረክ ነው።
ዴንማርክ በልማት ትብብር ፕሮግራሞቿና ተነሳሽነቶቿ አማካይነት የኢትዮጵያን የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ለመደገፍ የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት እንዳላት ተናግረዋል።
ከእነዚህም መካከል በውሃና ኢነርጂ ተቋማት መካከል በቀጥታ የልምድ ልውውጥ፣ የአቅም ግንባታ ማካሄድ፣ ብሔራዊ ፕሮግራሞችን መደገፍ፣ እንዲሁም የኢነርጂ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት ይገኙበታል ብለዋል።
በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ዘላቂ ኢንቨስትመንት፣ ፈጠራ፣ አስተማማኝ መረጃ፣ ጠንካራ ተቋማትና በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል የተጠናከረ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያና በዴንማርክ መካከል ያለው ትብብር ከልማት ድጋፍ በላይ ለንግድ አጋርነት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ለፈጠራ እና ለግል ኢንቨስትመንት ዕድሎችን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
ዴንማርክ የጋራ ዓላማዎቻችንን ለማሳካት ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከልማት አጋሮች፣ ከግሉ ዘርፍና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መሥራቷን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የሩዋንዳ አምባሳደር ቻርለስ ካራምባ በበኩላቸው፤ ውሃና ኢነርጂ ለሰው ልጆች ደህንነት፣ ለኢኮኖሚ ልማት እና ለአካባቢ ዘላቂነት አስፈላጊ ሀብቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ሀብቶች ያላቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ ቢኖርም፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በኢኮኖሚና በሕዝብ ቁጥር ዕድገት እንዲሁም ከዘላቂነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ምክንያት እየጨመረ የመጣ ጫና እየተጋፈጡ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ውሃንና ኢነርጂን በብቃት፣ በታዳሽነትና በዘላቂነት ማስተዳደር የውሃ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የኢነርጂ ተደራሽነትን ለማስፋፋትና ተግዳሮቶችን መቋቋም የሚችል የወደፊት ሁኔታ ለመፍጠር ወሳኝ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት የተሻሉ ተሞክሮዎችን ለመካፈል፣ አዳዲስ ፈጠራዎችን ለማስተዋወቅና በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመመርመር ዕድል እንደሚሰጥ አመላክተዋል።
Exit mobile version