Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ክልሉን በኢንዱስትሪና በኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልልን በኢንዱስትሪና በኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እየተሰራ ነው አሉ የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ፡፡
ቢሮው አዲስ ያለማውን “የኢንቨስትመንት ማኔጅመንት ሲስተም (IMS)” ወደ ተሟላ ትግበራ ለማስገባት የሚያስችል የፈጻሚዎች ሥልጠና ዛሬ አስጀምሯል።
አቶ እንድሪስ አብዱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ክልሉን በኢንዱስትሪና በኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች ውጤት አስገኝተዋል፡፡
በቀጣይም ግልጽ፣ ፍትሐዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለባለሀብቱ በመስጠት ክልሉን የኢንቨስትመንት ቀጣና ለማድረግ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ይህም ደንበኞች ለሚያቀርቡት የኢንቨስትመንት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና የሚስተዋሉ ችግሮችን በቀላሉ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከ17 በላይ አበይት አገልግሎቶችን መስጠት የሚችል “ዘመናዊ የኢንቨስትመንት ማኔጅመንት ሲስተም” ማልማት መቻሉን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
የአሁኑ ሥልጠና በሙከራ ትግበራ ላይ የነበረውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራር ወደ ተሟላ ትግበራ በማስገባት ፈጣንና ተጠያቂነት ያለው አሠራር ለማስፈን ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
Exit mobile version