Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ያለንን እምቅ ሀብት በመጠቀም ለህዝቡና ለሀገር የሚጠቅም ልማት ማረጋገጥ ይገባል – ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ያለንን እምቅ ሀብት በመጠቀም ለህዝቡና ለሀገር የሚጠቅም ልማት ማረጋገጥ ይገባል አሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ከአሪና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም ከጂንካ ከተማ ከተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በአካባቢው የልማት አፈጻጸም፣ በህዝቡ የልማት ፍላጎቶችና በሌሎች የህዝብ ጥቅም ጉዳዮች ላይ በጂንካ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንዳሉት፤ በአሪና ደቡብ ኦሞ የሚገኝ እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ የልማት ውጤት ለመቀየር እንሰራለን ብለዋል፡፡

በክልሉ ከሚገኙት 32 ብሔረሰቦች ውስጥ 16ቱ በአሪና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ የአካባቢውን እምቅ ሀብት በጋራ በመጠቀም ለህዝቡና ለሀገር የሚጠቅም ልማት ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ውይይቱ በሁለቱ ዞኖች መካከል ያለውን ትብብርና አብሮነት ከማጠናከር ባለፈ፤ በጋራ ለመሥራትና የህዝቡን የልማት ፍላጎቶች ለመመለስ ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

በአካባቢዎቹ ያለው የግብርና፣ የቱሪዝምና የማዕድን ሀብት እምቅ አቅም ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብቻ ሳይሆን፤ ለመላው ሀገሪቱ ትልቅ የልማት ሀብት ነው ብለዋል።

እንዲሁም አካባቢዎቹ የተለያዩ ባህሎች፣ የተፈጥሮ ሀብቶችና የኢኮኖሚ አቅሞች መገኛ በመሆናቸው፤ ለክልሉ ገጽታና ማንነት ወሳኝ መገለጫዎች ናቸው ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህንን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ የልማት ውጤት መቀየር ለአካባቢው ሕዝብ የኑሮ መሻሻል፣ ለክልሉ እንዲሁም ለሀገር አጠቃላይ ዕድገት የሚያበረክተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

Exit mobile version