አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትርፍ ስሌታቸውን በጦርነት አዙሪት ያደረጉ፣ ያለእኔ ሀገር መቀጠል የለባትም የሚሉ እንደ ህገወጡ የህወሓት ያሉ ቡድኖች በተደጋጋሚ ትንኮሳ ቢያደርጉም ሲወድቁ እንጂ ሲሳካላቸው አይታይም፡፡
ህገወጡ የህወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ የተወሰደበት ወታደራዊ ርምጃ የህገወጡ ህወሓት ቡድን የመጀመሪያ ሽንፈት የሚያሳይ ነው፡፡
በዚህም የፌዴራል መንግሥት በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ዋና ከተማዋን መቐለን መቆጣጠር ችሎ ነበር፡፡
ሌላው ጦርነቱ ከትግራይ አልፎ ወደ ሌሎች ክልሎች በተዛመተበት ወቅት በህብረትና በአንድነት ሆነው ድል መንሳታቸውን፣ የሀገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል ሲሰራ የነበረውን ህገወጡን ህወሓት የተለያዩ ክልሎች ከፌደራል መንግሥት ጋር በመሆን ጦርነቱን የቀለበሱበትና ህገወጡን ቡድን የሽንፈት ጽዋውን እንዲጎነጭ ያደረጉበት ነበር፡፡
በዚህም ሂደት የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ በመቆም ህብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን አሳይተዋል፡፡
ለረጅም ጊዜያት ህዝቡን የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ማስጠበቂያ ሲያደርገው የቆየው ህገወጡ ህወሓት በባህሪው ዓላማ መር ባለመሆኑ፤ በውስጡ ያሉት እርስ በርሳቸው የሚቆሙበትና የሚታመኑበት የጋራ ግብ የላቸውም፡፡
መንግሥት ለትግራይ ህዝብ ሰላም የሚጨነቅና ለድርድርም ቀናኢ ፍላጎት ያለው በመሆኑ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ማካሄዱ ይታወሳል፡፡
ነገር ግን በተደጋጋሚ ከሽንፈቱ የማይማረው ሕገወጡ የህወሓት ቡድን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ወደጎን በመተው በስምምነቱ ላይ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን መጣስን መርጧል፡፡
ትጥቅ መፍታት ሲገባው የጦር መሳሪያ ግዢና የወጣቶች አስገዳጅ ምልመላ ላይ ተሳትፏል፡፡ በስምምነቱ መሰረት የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለመሻር ሞክሯል፡፡ መንግሥትን ለመጣልና ሀገር ለመረበሽ ከሚያግዙ የውስጥና የውጪ ኃይሎች ጋር ይሰራል፡፡
ህገወጡ የህወሓት ቡድን በቅርቡ ትንኮሳ ያደረገ ቢሆንም የሀገር መከላከያ ሠራዊት በጥቂት ቀናት ውስጥ ህገወጡን የህወሓት ቡድን በመበታተን ከትግራይ የሰላም ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ተደብቀው የነበሩ መሳሪያዎችን፣ ተሸከርካሪዎችንና ጥይቶችን ጭምር በቁጥጥር ስር በማዋል የትግራይ ክልል ከተሞችንም ተቆጣጥሯል፡፡
ዛሬ ላይ ህገወጡ የህወሓት ቡድን በትግራይ ያወደማቸውን መሠረተ ልማቶች የመመለስ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን፤ ተማሪዎችም ወደ መደበኛ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡
የህገወጡ ህወሓት ቡድን መገለጫው በሌሎች ህልውና ውስጥ ተደብቆ ነገር ግን እኔ ብቻ በሚል ትምክህት ሁሉን ብቻውን ለመጠቅለል የሚፈልግ ነው፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በ119ኛው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ክብረ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን አራት ጊዜ እንቅፋት የመታው ፍጡር ነው ብለዋል፡፡
በቤተልሔም ግርማ

