አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ተጠሪ እና የሰብዓዊ ድጋፍ ዋና አስተባባሪ ኦዞንያ ኦጂሎ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ ቀጣናዊ፣ አካባቢያዊና ሃገራዊ ሰላምና መረጋጋት የማጠናከር አስፈላጊነትና ትብብሮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ኦዞኒያ ኦጅሎ (ዶ/ር) ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር የነበራቸውን ቆይታ አስመልክተውም ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት የመንግሥታቱ ድርጅት የሚደግፈው መሆኑንና ለዚህም አላማ ስኬት ከጎኗ እንደሚቆም ኦዞኒያ ኦጅሎ (ዶ/ር) ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ባደረጉት ውይይት አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ እንዳለበት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ድንበሬ ተጥሶብኛል ብላ ያቀረበችው ጉዳይ በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፈታት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡
ህግና ሥርዓትን ማረጋገጥ፣ የዲዲአር ሂደትን መተግበር፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው መመለስና የህዝብ እውቅና ያለው ህገመንግሥታዊ የሲቪል አስተዳደርን ወደ ቦታው በመመለስ ሂደት የመንግሥታቱ ድርጅት ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆምና መንግሥትን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
አሁን የተገኘው ሰላም በኢትዮጵያ የተጀመረውን የማህበራዊ ኢኮኖሚ የለውጥ እመርታ ለማሳደግና በሃገሪቱም የተረጋጋ ሁኔታ ለማምጣት ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊና ሰላማዊ ተግባራት እንዲጠናከሩ ቁርጠኛ መሆኑንና እያደረገ ላለው ትብብርም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ይህን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት አዲስ አበባ መጥተው ከኢትዮጵያ መንግሥት የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ አካባቢያዊ ሰላም እንዲጠናከር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ከጎኗ እንደሚቆም ማረጋገጣቸው ይታወሳል።

