አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ስም የነበራት አሰብ በአንድ ወቅት የቀጣናው ንግድ፣ ትራንስፖርት እና የኢንዱስትሪ ማዕከል ሆና አገልግላለች።
የከተማዋ የኢኮኖሚ እንስቃሴ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ የወደብ አገልግሎት፣ የባንክ እና የትራንዚት ድርጅቶች መናኸሪያ በመሆኗ ከልዩ ልዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ ዜጎች ሁለተኛ ቤታቸው አድርገዋት ኖረዋል።
የቀድሞው የአሰብ ምክትል ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሊበን እንደሚገልጹት÷ አሰብ ከኢትዮጵያ በተለየችበት ወቅት የነበራትን የኢኮኖሚ ግርማና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ አጥታለች።
በአንድ ወቅት የብልጽግናና የሥራ ዕድል ማዕከል የነበረችው ከተማ ዛሬ ጭር ያለች እና ሰው አልባ እየሆነች የመጣች መሆኗንም ያስረዳሉ።
አሰብን ከባሕር ዳር፣ ከጎንደርና ከሐዋሳ ካሉ ከተሞች ጋር ስናነጻጽር በከተሞቹ የልማት ጉዞ መካከል ያለው ልዩነት አሰብ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደተጓዘች በግልጽ ያሳያል ያሉት የቀድሞ ምክትል ከንቲባው ይህ ለውጥ የከተማዋን አካላዊ ገጽታ ብቻ ሳይሆን፤ በዚያ ይኖሩና ይሠሩ የነበሩ በርካታ ዜጎችን ሕይወትም እንደነካ ይገልጻሉ።
በከተማዋ ሠርተው ሀብትና ንብረት ያፈሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከቤትና ንብረታቸው መለየታቸውን አንዳንዶችም የደረሱበት ሳይታወቅ ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መዳረጋቸውን አብራርተዋል።
የሻዕቢያ አገዛዝ ስልጣን ከተቆጣጠረ እና አሰብ ለኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት ካቆመች በኋላ፣ የከተማዋ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ውድቀት ተዳርጋለች።
ኢትዮጵያም የነበራትን ሕጋዊ የሆነ ስትራቴጂካዊ ባለቤትነት በውስጥ ባንዳዎች ሴራ እና በውጭ የታሪክ ጠላቶች የጥቅም ተፅዕኖ ምክንያት እንድታጣ መደረጉ ሀገራችን ለከፍተኛ ስትራቴጂካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንድትዳርግ ምክንያት ሆኗል።
ይህ ቁስል የአንድ ትውልድ አሳዛኝ ገጽታ ሆኖ የሚታወስ ነው።
ለቀጣናው ሀገራት ከፍተኛ የኢኮኖሚና የደህንነት ጥቅም ያለው የቀይ ባህር በየጊዜው ከሚቀያየሩ የመንግሥታት ተግባራት ባሻገር የኢትዮጵያ ህልውና፣ የብሔራዊ ደህንነት እና የትውልድ ዘላቂ ዋስትና መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባው ነው።
ታሪካችን እንደሚነግረን ከአክሱም የስልጣኔ ዘመን ጀምሮ እንደ አጼ ዮሐንስ እና ራስ አሉላ አባ ነጋ ያሉ ታላላቅ መሪዎች እና አርበኞች የቀይ ባህር ወሰንን ለማስጠበቅ እና የሀገሪቱን ታሪካዊ የባህር በር ለማስከበር ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል።
የባህር በር ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ ሂደትን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በመደገፍ እና ከመንግሥት ጎን በመቆም ታሪካዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
በዮናስ ጌትነት

