Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የቆመው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲዋ ለሰላምና ለትብብር ክፍት የሆነ አካሄድን ትከተላለች፤ ሉዓላዊነቷን ግን ለድርድር አታቀርብም፡፡
አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ኢትዮጵያ ሁሌም ቅድሚያ የምትሰጠው ለውይይትና ለድርድር ሲሆን፤ የጋራ ተጠቃሚነትንም መሰረት በማድረግ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን በራሷ ሀብትና በሕዝቦች ትዕግስት የታከለበት የደምና ላብ ትጋት ለውጤት አብቅታለች፡፡
ዜጎችን ከድህነት ማውጣት የተገባቸውንም ኑሮ እንዲኖሩ ማስቻልና ለጎረቤቶችም ጭምር መትረፍ የዚህም ዓላማ ነው፡፡ የዚህም ውጤት በተጨባጭ የታየና ለጎረቤቶችም የኃይል አቅርቦትን ያተረፈ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ምንጭ ብትሆንም እንደ ግብፅና ሱዳን ካሉ ሀገራት ጋር ድርድር ስታደርግና ሌሎችን በማይጎዳ መልክ የመጠቀም ፍላጎቷን ስታሳይ ቆይታለች፡፡ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር ሲኖርባትም እንዲሁ አድርጋለች፡፡
የባሕር በር ጥያቄም ከ130 ሚሊየን ህዝብ በላይ ለያዘች ሀገር የህልውናዋ ጉዳይ እንጂ የቅንጦት ጥያቄ አይደለም፡፡ ወጪና ገቢ ንግዷን በጎረቤት ሀገራት ወደቦችና በመልካም ፈቃደኝነታቸው ላይ ተመስርታ ማካሄዷ የኢኮኖሚ ህልውናዋን የሚገዳደር ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት ስትጠይቅም በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ ተመስርታ፣ ኃይልን ሳይሆን የጋራ ጥቅምን መሠረት አድርጋ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በምታደርገው ጥረት የኢኮኖሚ አቅምን መገንባት ተፅዕኖ ፈጣሪነት አቅምን የሚያሳድግ በመሆኑ፤ የኢኮኖሚ አቅሟን ለማስጠበቅ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ሚዛኑን የጠበቀ ግንኙነት እየገነባች ትገኛለች፤ የብሪክስ አባል በመሆኗም ከሀገራት ጋር ያላትን አጋርነት አስፍታለች፡፡
ሀገራት አጋርነቶችን ሲመሰርቱ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ የመስራት እድሎችን ያሰፋል፤ ለኢትዮጵያም የኢንቨስትመንት፣ የንግድ በሮችን ይከፍታል፣ ይህም ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅምን ለመገንባት ወሳኝ ሚናን ይጫወታል፡፡
በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የቀጣናዊ ትብብር ተጨባጭ ጥቅም እንዳለው ለምታምነው ኢትዮጵያ ልማቷ ለጎረቤት ሀገራት የስጋት ሳይሆን በጋር የመልማት እድልን ይዞ የሚመጣ ነው፡፡
ይህ የኢትዮጵያ ሚዛንን ያስጠበቀ አካሄድ ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለአህጉሩም ብሔራዊ ጥቅምን በጽናት የማስከበር እንዲሁም የሰላምና በትብብር አብሮ የማደግ ተምሳሌት የሚሆን ተግባር ነው፡፡
በቤተልሔም ግርማ
Exit mobile version