Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞዛምቢክ ናካላ ከተማ አዲስ በረራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞዛምቢክ ናካላ ከተማ አዲስ በረራ ጀምሯል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ በዚሁ ወቅት÷ ኢትዮጵያና ሞዛምቢክ በፓን አፍሪካኒዝም መርህ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ትስስር እንዳላቸው ገልጸዋል።
ወደ ናካላ ከተማ የተጀመረው በረራ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር አስፈላጊ ሚና አለው ብለዋል።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ከጣና ፎረም ጎን ለጎን በጋራ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰው ይህም ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች የሚኖራቸውን ትብብር ለማስፋት መሠረት የሚጥል መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የሞዛምቢክ አምባሳደር ኑኖ ቶማስ በበኩላቸው÷ አዲሱ በረራ የሁለቱን ሀገራት የቱሪዝም፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳለጥ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በሁለቱ ሀገራት ያሉ ባህላዊ ትውፊቶችንና ሀብቶችን ለዓለም ለማስተዋወቅ አዲሱ የአየር ትስስር ጠቃሚ አጋጣሚ በመፍጠር በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነትም ለማጠናከር አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ ረታ መላኩ በበኩላቸው፣ ናካላ በሞዛምቢክ የአየር መንገዱ ሦስተኛ መዳረሻ መሆኗን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ የአፍሪካ ሀገራትን በማስተሳሰር የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም እንቅስቃሴን ለማስፋፋት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወደ ናካላ የተጀመረው በረራም የዚሁ አህጉራዊ ዓላማ አካል መሆኑን አስረድተዋል።
በዛሬው ዕለት የተጀመረው በረራ፣ አየር መንገዱ በሞዛምቢክ ከማፑቶና ቤይራ በመቀጠል ሦስተኛው መዳረሻው ነው።
Exit mobile version