Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጣና ፎረም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን የማስተናገድ አቅሟን የሚያጠናክር ነው – አምባሳደር ነብያት ጌታቸው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) 12ኛው የጣና ፎረም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን የማስተናገድ አቅሟ እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ ነው አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው።
አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ 12ኛው የጣና ፎረም በውቢቷ ባህርዳር ከተማ ተካሂዶ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አንስተዋል፡፡
የአፍሪካ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በፎረሙ መታደማቸውን ጠቁመው፤ በአፍሪካ ሰላም፣ ደህንነት እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ዙሪያ ምክክር መደረጉን ገልፀዋል፡፡
የጋና ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ፣ የቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ፣ የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት ዳንኤል ቻፖ እና የኬንያውን ምክትል ፕሬዚዳንት ኪቱሬ ኪንዲኪን ጨምሮ በርካታ እንግዶች መገኘታቸውን አስታውሰዋል።
በመሪዎች ደረጃ ከፍተኛ ውክልና መኖሩ እና በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ጠንክር ያሉ ሃሳቦች መነሳታቸው የዘንድሮውን የጣና ፎረም ለየት እንደሚያደርገው አብራርተዋል፡፡
በመድረኩ አፍሪካ የኢኮኖሚ እና የምግብ ሉዓላዊነትቷን ካላረጋገጠች ለበርካታ ችግሮች እና ጫናዎች ልትዳረግ እንደምትችል መነሳቱን ገልጸው በመድረኩ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያደረገቻቸውን ጥረቶች ማቅረቧን ጠቁመዋል፡፡
የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ካልተረጋገጠ የፖለቲካ ነፃነት ሊኖር አይችልም ያሉት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ ይህን በመረዳት የምግብ ዋስትናና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አበክራ እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ፎረሙ ለኢትዮጵያ ኮንፈረንስ ቱሪዝም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመው፤ ፎረሙ ከአዲስ አበባ ውጭ በውቢቷ ባህርዳር መካሄዱ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን የማስተናገድ አቅም እንዳላት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2025 እስከ 2026 ባሉት ጊዜያት 204 ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ማስተናገዷን ጠቅሰው፤ የጣና ፎረም ተጨማሪ የማስተናገድ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
በሚኪያስ አየለ
Exit mobile version