Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የ’ሳሙ ኤታ’ ጸጋን የመለየትና የመጠቀም ጥበብን ያስተምራል – የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የየም ብሔረሰብ የመድኃኒት ለቀማ ‘ሳሙ ኤታ’ ጸጋን የመለየትና የመጠቀም ጥበብን ያስተምራል አሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)፡፡

የየም ብሔረሰብ ባህላዊ የመድሃኒት ለቀማ ‘ሳሙ ኤታ’ በየም ዞን ፎፋ ወረዳ በቦር ተራራ ተካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት÷ የየም ብሔረሰብ ባህላዊ የመድሃኒት ለቀማ በክልሉ ለኢትዮጵያዊ የስልጣኔ መሰረት የሚሆኑ ማህበረሰባዊ ጥበቦች እንዳሉ ያሳያል።

ይህ ጥንታዊ የመድኃኒት ለቀማ ባህል የማስተዋልና የፈጠራ እንዲሁም ጸጋን የመለየትና የመጠቀም ጥበብን ያስተምራል ብለዋል፡፡

ይህ ባህል ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እና ለህብረተሰቡ ጤና አስተዋፅኦ እንዲኖረው ለማድረግ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይሁን አሰፋ በበኩላቸው÷ በዞኑ በዕጽዋት ሀብት በበለፀገው የቦር ተራራ ላይ ለመድሐኒትነት የሚውሉ 210 እጽዋት እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በየዓመቱ ጥቅምት 17 የብሔረሰቡ አባላት ከተራራው ላይ ለመድሐኒት የሚሆኑ እጽዋትን እንደሚለቅሙ ተናግረዋል፡፡

የተለቀመው እጽዋት ተቀምሞ አዋቂዎች በሚሰጡት ምክረ ሀሳብ መሰረት የተለያዩ በሽታዎችን ለመፈወስ እንደሚውል ገልጸው፤ ሰው እና እንስሳትን ለመፈወስ የሚውለው ይህ መድሐኒት የአገልግሎት ጊዜው አንድ ዓመት ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል።

የመድሐኒት ለቀማው የሀገር በቀል እውቀት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው÷ ‘ሳሞ ኤታ’ የየም ማህብረሰብ ሰው እና እንስሳትን ከተለያዩ በሽታዎች ጠብቆ ያቆየበት ጥበብ መሆኑን ተናግረዋል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በወርቅአፈራው ያለው

Exit mobile version