Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ በራስ አቅም የመቆም ተምሳሌትነት ለአፍሪካ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ አህጉር ከዘመናት የውጭ ጥገኝነት፣ የዕርዳታ እጅ የመዘርጋት ባህል እና በሌሎች ውሳኔ ሥር ከመውደቅ ተላቃ፤ በገዛ ሀብቷ፣ በገዛ አቅሟና በዜጎቿ የተቀናጀ ጥረት ታሪኳን በአዲስ መልክ የመጻፍ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።
በዚህ ታሪካዊ አህጉራዊ የመነሳት ጉዞ ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያ የሐሳብ መነሻ በመሆን ብቻ ሳይሆን፣ በተግባር አሳይታ ተምሳሌት መሆን የቻለችበትን የልማት መስመር በመቀየስ የመሪነት ሚናዋን በግልጽ እያስመሰከረች ትገኛለች።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የቀድሞ ሊቀ መንበር ንኮሳዛ ድላሚኒ-ዙማ እንዳነሱት፤ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ለመልማት የምታደርገው ጥረትና በኃይል ዘርፍ የወሰደቻቸው ድፍረት የተሞላባቸው ውሳኔዎች ለአፍሪካ እድገት ትልቅ ተምሳሌት ናቸው፡፡
ይህ ምስክርነት፤ ሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ያሳለፈቻቸው ታሪካዊ ውሳኔዎችና ያከናወነቻቸው ዘላቂ የልማት ሥራዎች፣ አፍሪካውያን በእጃቸው ባለው ሀብትና መሬት ላይ በራሳቸው ውሳኔ ታሪክን መቀየር እንደሚችሉ ማሳያ በመሆን ብሩህ ተስፋን ፈንጥቀዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ጀምሮ የነበራትን የነፃነት ምልክትነት አሁን ደግሞ ወደ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ የበላይነት በመቀየር ለአህጉራዊ አንድነትና ሰላም የምታበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ የላቀ ነው።
የድላሚኒ-ዙማ መልዕክት ከፊታችን በሚደረገው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ አፍሪካውያን የሚጠብቁትን ኢትዮጵያ የሚኖራትን የመሪነት ሚና ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው፡፡
ሀገሪቱ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደመሆኗ የተጣለባትን ታሪካዊ ኃላፊነት በጥበብ በመረዳት፣ አህጉሪቱን በመልካም ተሞክሮ የመምራት፣ የጋራ ዕድገትን እውን የማድረግና የተቀናጀ የሰላም ግንባታ ሂደቶችን በግንባር ቀደምትነት የመደገፍ አደራዋን በብቃት እየተወጣች ትገኛለች።
ይህ ታሪካዊ አደራ የሚጠይቀውን የጽናትና የውሳኔ ቁርጠኝነት ሀገሪቱ በተግባር ያሳየችበት በርካታ ማሳያዎች አሏት።
ድላሚኒ-ዙማ ይላሉ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውጫዊ ድጋፍን የመጠበቅን ባህል በመስበር በራስ አቅም መቆም እንደሚቻል የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው።
እውነትም፤ የዚህ አህጉራዊ ትንሣኤና በራስ አቅም የማደግ ውሳኔ ዋነኛ ሕያው ማሳያ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ውጫዊ ድጋፍንና የውጭ ረድኤትን የመጠበቅን የቆየ ስነ-ልቦናዊ ገደብ አፈር ድሜ ያበላ ታላቅ ክስተት ነው።
ድላሚኒ-ዙማ ይቀጥላሉ፤ ኢትዮጵያውያን ውጫዊ ድጋፍን ሳይጠብቁ የህዳሴውን ግድብ በገዛ አቅማቸው መገንባታቸው እጅግ የሚደነቅ ነው።
እንደ እሳቸው አገላለጽ፤ ኢትዮጵያውያን በውስጥና በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻቸውን በማስተባበር፤ የገንዘብ፣ የዕውቀት፣ የሙያ እና የጉልበት አዋጮች በመሆን ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት በገዛ አቅማቸው ብቻ መገንባታቸው በአፍሪካ የልማት ታሪክ ውስጥ ተአምርን ያስመለከተ አዲስ ምዕራፍ ነው።
ይህ ርምጃ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው አቅም መፍታት እንደሚችሉ ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን፣ ለአህጉሪቱ ሕዝቦች የታላቅነትና በራስ የመተማመን ስነ-ልቦናን ያበሰረ ድል ነው።
የአፍሪካ የዕድገት አድማስ የሚሰፋው፣ ድህነት የሚወገደውና ዘላቂ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው አህጉሪቱ በገዛ ሀገራዊና አህጉራዊ አቅሟ ላይ ሙሉ እምነት ስትጥል ብቻ ነው።
እዚህ ጋርም ዙማ አንድ ምክር አላቸው፤ የአፍሪካ መሪዎች የኢትዮጵያን በራስ የመተማመን እሳቤ እና የመከወን አቅም እንደ መልካም ተሞክሮ ሊወስዱት ይገባል፤ አህጉራዊ ዘላቂ እድገት ሊረጋገጥ የሚችለው በገዛ ሀገራዊና አህጉራዊ አቅም ላይ ሙሉ እምነት ሲኖር ብቻ ነው።
ምክራቸው ግልጽ ነው፤ የአፍሪካ መሪዎችና ሀገራት የኢትዮጵያን በራስ የመተማመን እሳቤ፣ የቁርጠኝነት መንፈስና የመከወን አቅም እንደ ታላቅ አርአያነት በመከተል፣ የየሀገራቸውን ሕዝባዊና ተፈጥሮአዊ አቅም አቀናጅተው ወደፊት ላለው የብልፅግና ጉዞ መገስገስ ይኖርባቸዋል።
በዜጎች አቅም የምትደገፍ፣ አህጉራዊ የኃይልና የኢኮኖሚ ትስስሯ የተጠበቀ፣ ሰላማዊና በራስ አቅም የበለፀገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ኢትዮጵያ የጀመረችው የመሪነት ጉዞ ለአህጉሪቱ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ነፃነትና ሁለንተናዊ ትንሣኤ ጽኑ መሠረት ሆኖ ይቀጥላል።
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version