በዲፕሎማሲው መስክ አፍሪካና ሩሲያ በጊዜ ሂደት እያደገ የመጣ አጋርነት መሥርተዋል አሉ የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማርያ ዛካሮቫ።
ቃል አቀባይዋ እንዳሉት÷ አጋርነቱ ሁሉን አቀፍ ባሕርይ ያለውና በወንድማማችነት መርህ ላይ የተመሠረተ ነው።
አፍሪካውያንም ሉዓላዊነታቸውን በሚያከብርና በራሳቸው ውሳኔ የሚመሩበትን ግንኙነት ለመመሥረት እየተጉ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በተለይም በምግብ ራስን የመቻል አጀንዳ የአፍሪካን ውስጣዊ አቅም ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
ሀገራት የራሳቸውን አቅም ሲያጠናክሩ ጫናዎችን ለመቋቋምና ከራሳቸው ጥቅም ጋር የማይጣጣሙ ሐሳቦችን ወይም ውሳኔዎችን ለመቃወም የበለጠ አቅም እንደሚኖራቸው አስረድተዋል።
ሆኖም ቀጣይነት ያለው ጥረት እንደሚያስፈልግ አንስተው ሀገራት በትብብር ለመሥራት እንደ አፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ያሉ ተነሳሽነቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች አህጉር መሆኗን በማንሳት ሀብቷን በአግባቡ በመጠቀም ለዜጎቿ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ማረጋገጥ የአፍሪካውያን ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል።
ዜጎችም ከመንግሥታቸው ጋር በመተባበር ለሀገራቸው እድገትና ለሕዝባቸው ብልጽግና የበኩላቸውን ማበርከት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መንግሥታት ያላቸውን አቅም በማሳደግ ወጣቶችን ማብቃትና በእውቀት፣ በክህሎትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእድገት መሠረት መገንባት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
ሩሲያም በእነዚህ የአፍሪካ የእድገት ጥረቶች ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች የበኩሏን ድጋፍ ማድረግ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
በአሸብር ካሳሁን

