Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጠንካራ መከላከያ ሠራዊት – ለሀገራዊ ልማትና ለቀጣናዊ ዘላቂ ሰላም

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘመናዊ የጂኦፖለቲካ እና የጸጥታ ጥናቶች በጋራ ከሚስማሙባቸው ጉዳዮች አንዱ ልማትና ዘላቂ ሰላም ያለ አስተማማኝ የመከላከያ ኃይል ሊታሰብ እንደማይቻል ነው።
የአንድ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ጥንካሬ ድንበር ከማስከበር ባለፈ ለኢኮኖሚ ዕድገት ዋስትና የሚሰጥ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚያበረታታ እና ለቀጣናዊ ትስስርም መሠረት እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሀገራዊ ዕድገት እንዲሁም ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ መረጋጋት እያበረከተ ላለው ቁልፍ አስተዋጽኦ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ እውቅና አስገኝቶለታል።
የተለያዩ የዘርፉ የምርምር ተቋማት ጥናቶች እንደሚገልጹት፣ ወታደራዊ ጥንካሬ እና የኢኮኖሚ ልማት የማይነጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ያሉ የሀገር ሀብቶችን ከውስጥ እና ከውጭ ጥቃቶች በመጠበቅ የሀገሪቱን የልማት ጉዞ ለማስቀጠል አስችሏል።
ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅሞቿን ከማስከበር ባሻገር ቀጣናዊ ሰላምን በማስፈን የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
ዘላቂ ሰላም መፈጠሩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች በራስ መተማመን ከፍ እንዲልና ለውጭ ቀጥታ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ትስስር እንዲፈጠርና የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና (AfCFTA) ተግባራዊ እንዲሆንና የንግድ ግንኙነት እንዲጠናክር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው፡፡ ይህን ኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱትሪ ፓርኮቿ ነጻ የንግድ ቀጣና በማስፋፋት በተግባር እያሳዬች ትገኛለች፡፡
ይህ ተግባራዊ ሆኖ ፍሬ የሚያፈራው ታዲያ ቀጣናዊ ሰላም ሲረጋገጥና ልማት ሲጠናከር ብቻ ነው፡፡ እነዚህን ሁለት ጉዳዮች ለማሳካት የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሀገር ውስጥ እና በቀጣናው አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንደ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ሱዳን ባሉ የቀጣናው ሀገራት ያካሄዳቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ለቀጣናዊ ትስስር እና ትብብር መሰረት የሚጥሉ ናቸው። ሰራዊቱ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀራረብ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር እንደ አል-ሻባብ ያሉ ቀጣናዊ የአሸባሪ ቡድኖችን በመዋጋት ረገድ አርአያነት ያለው ሚና ተጫውቷል።
ይህ ቀጣናዊ የጸጥታ ዋስትና ደግሞ ለወደፊቱ የአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ውህደት መንገድ ጠራጊ ነው። የጂኦፖለቲክ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የንግድ፣ የትራንስፖርት እና የኢነርጂ ትስስሮች እውን ሊሆኑ የሚችሉት በአስተማማኝ ሰላም ላይ የተመሰረተ ድንበር ሲኖር ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በቀጣናው የሚያስፍነው ሰላም ሀገራት እርስ በእርስ እንዲቀራረቡና የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋገጡ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ሉዓላዊነት ከማስከበር ባሻገር፣ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልጽግና እንዲሁም ማህበራዊ ሽግግር ወሳኝ ሚና አበርክቷል ፤ እያበረከተም ይገኛል።
በቴዎድሮስ ሳህለ
Exit mobile version