አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የረጅም ጊዜ ያስቆጠረ የዲፕሎማሲ፣ የወታደራዊ፣ የባህል እና የፖለቲካ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተጀመረው በፈረንጆቹ 1898 ሲሆን፣ የመጀመሪያው የሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ በአዲስ አበባ ተቋቁሟል።
ከዚያን ጊዜ እንስቶ እስካሁን የሀገራቱ ግንኙነት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ትብብሮች ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡
የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗን ተከትሎ ፈጣን ዕድገትና ስትራቴጂካዊ ሽግግር እያሳየ የሚገኝ ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2025 የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ ከ435 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ደርሷል፡፡
ኢትዮጵያ ከሩሲያው የመንግሥት የኒውክሌር ተቋም ሮስአቶም ጋር በመሆን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮግራም ለመገንባት የሚያስችል ፍኖተ-ካርታ መፈራረሟ ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም በግብርና እና አግሮ-ፕሮሰሲንግ ትስስር፣ በፋይናንስና ዲጂታል ክፍያ ሥርዓት እንዲሁም በኢንቨስትመንት ዘርፎች ትብብራቸውን እያጠናከሩ ይገኛሉ፡፡
በተመሳሳይ ሁለቱ ሀገራት ባላቸው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሩሲያ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የነፃ ትምህርት ዕድል እየሰጠች ሲሆን እስካሁን ድረስ ከ20 ሺህ እስከ 25 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች ተምረው ተመርቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የረጅም ዘመን የወንድማማችነት ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ይህ የጋራ ክርስቲያናዊ ቅርስ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መቀራረብ ዋነኛ መነሻ እንደነበርም ይነገራል፡፡
ሩሲያ ከፈረንጆቹ 2023 ጀምሮ አማርኛ ቋንቋ ትምህርት በሞስኮ ትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ ማድረጓም የሁለቱ ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የበለጠ እየተጠናከረ መምጣቱን የሚሳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ ሙሉ አባል መሆኗን ተከትሎ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ተነቃቅቷል።
በተለይም በወጣቶች መድረክ፣ በስፖርት፣ በቱሪዝም፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ (ለምሳሌ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) እና በባህል ፌስቲቫሎች ላይ የሚደረጉ የጋራ ተሳትፎዎች አድገዋል።
በተጨማሪም በመከላከያ ዘርፍ የኢትዮጵያና የሩሲያ ወታደራዊ ግንኙነት ረጅም ታሪክ ያለውና በአሁኑ ወቅት ወደ ስትራቴጂካዊና ወታደራዊ-ቴክኒክ አጋርነት ያደገ ጠንካራ ግንኙነት ነው።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ስትራቴጂክ ትብብር ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ፤ ግንኙነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡
ጥቅምት 18 እና 19 በሚካሄደው 3ኛው የሩሲያ – አፍሪካ ጉባኤ ከቀጣናዊ ውይይቶች በተጨማሪ ኢትዮጵያና የሩሲያን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ምክክሮች ይደረጋሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
በሚኪያስ አየለ

