አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)የመደመር መንግሥት መጽሐፍ እንደሚያብራራው፣ ልማት ማለት ከአካላዊ ግንባታ በላይ የሆነ፣ ሰውን ማዕከል ያደረገ፣ ሀብቶችን በተቀናጀ መንገድ የሚጠቀም፣ የሕዝብ ተሳትፎን የሚያጠናክርና የጋራ ብልጽግናን የሚያሳድግ ሂደት ነው።
በዚህ እሳቤ መሠረት የከተማ ልማት መንገዶችን፣ ሕንፃዎችንና መሠረተ ልማቶችን ከመገንባት ባለፈ፣ የነዋሪዎችን የኑሮ ጥራት ማሻሻል፣ የኢኮኖሚ አቅምን ማሳደግ፣ ተፈጥሯዊ ሀብቶችን መጠበቅና ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፍ ዘላቂ ከተማ መፍጠርን ያካትታል።
በዚህ የልማት አቅጣጫ አዲስ አበባ የመደመር መርሆችን ወደ ተጨባጭ ሥራ በመቀየር የለውጥ ጉዞዋን እያስቀጠለች ትገኛለች። በኮሪደር ልማት፣ በወንዝ ዳርቻ ልማት፣ በከተማ ውበትና በአረንጓዴ ልማት የሚከናወኑት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ ለነዋሪዎች የተሻለ የኑሮና የአገልግሎት አማራጭ ለመፍጠር ያግዛሉ።
በተለይም የከተማዋን ወንዞች ከብክለት በማጽዳት፣ የተፈጥሮ ሚዛናቸውን በማስመለስና የወንዝ ዳርቻዎችን ለሕዝብ ምቹ ወደሆኑ ስፍራዎች በመቀየር የአካባቢ ጥበቃንና የነዋሪዎችን ጥቅም ማጣጣም እየተቻለ ነው።
ወንዞች የቆሻሻ መጣያ ከመሆን ወጥተው የውበት፣ የመዝናኛና የኢኮኖሚ ዕድል ምንጭ እንዲሆኑ የሚደረገው ጥረት፣ ያሉ ሀብቶችን በአግባቡ በመጠቀም ለሕዝብ ጥቅም የማዋል አስፈላጊነትን ያሳያል።
የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ለንግድ፣ ለአገልግሎት፣ ለመዝናኛና ለሌሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች አዳዲስ ዕድሎችን እየፈጠሩ ነው። ይህም የከተማዋን ኢኮኖሚ ከማነቃቃት ባለፈ፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ለማስፋት፣ የሥራ ዕድሎችን ለማበራከትና የምርታማነት አቅምን ለማጠናከር መሠረት ይሆናል።
ስለዚህ የልማት ውጤት የሚመዘነው በተገነቡ መሠረተ ልማቶች ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ በሚፈጥረው የሥራ ዕድል፣ በሚያሻሽለው የኑሮ ጥራትና በሚያስገኘው ዘላቂ ሕዝባዊ ጥቅም ጭምር ነው።
የመደመር እሳቤ ከሚያጎላቸው መርሆች አንዱ የተለያዩ አቅሞችን፣ ሀብቶችንና ዕውቀቶችን በማቀናጀት የተሻለ የጋራ ውጤት ማምጣት ነው።
ይህ በከተማ ልማት ሲተገበር፣ የመንግሥትን አመራር፣ የባለሙያዎችን ዕውቀት፣ የግሉን ዘርፍ አቅምና የሕዝብን ተሳትፎ በማጣመር ውጤታማ ሥራ ማከናወንን ይጠይቃል።
በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ የልማት ተሞክሮ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ በተቀናጀ ዕቅድና በተናበበ አፈጻጸም የጋራ ጥቅምን ማሳካት እንደሚቻል የሚያሳይ ልምድ መሆኑን ከከንቲባ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በዚህ አቅጣጫ አዲስ አበባ የመደመር መንግሥት የከተሞች ልማት ዕይታ በተግባር የሚገለጽባት ከተማ ከመሆኗም በላይ፣ ለሌሎች ከተሞች ሊጋራ የሚችል ተሞክሮ እያፈራች ነው። የዚህ ተሞክሮ ዋና ትርጉም የከተማ ልማት ሰውን፣ አካባቢንና ኢኮኖሚን በአንድነት ሲያስብ ዘላቂና ውጤታማ እንደሚሆን ማሳየቱ ነው።
ከተማ የምትመስለው በሕንፃዎቿ ብቻ ሳይሆን፣ ለነዋሪዎቿ በምትፈጥረው የኑሮ ዕድልና በምታቀርበው አገልግሎት ጭምር ነው። አዲስ አበባም የዛሬውን ልማት የነገ ብልጽግና መሠረት በማድረግ፣ ለነዋሪዎቿ የተሻለ ኑሮ የሚፈጥርና ለቀጣይ ትውልድ የሚበጅ ከተማን በጋራ የመገንባት ጉዞዋን ቀጥላለች።

